ኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሦስት ወረዳዎች ከ34 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እየመገበ መኾኑን አስታወቀ፡፡

48

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ በኾነው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሦስት ወረዳዎች ከ34 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እየመገበ መኾኑን አስታውቋል፡፡ በትምህርት ቤት ምገባው ከምግብ ባሻገር የተማሪዎችን የትምህርት ቁሳቁስ እና ለሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንደሚያሰራጭም አስታውቋል፡፡

በበርካታ አካባቢዎች የተማሪ ምገባ አገልግሎት ባለመኖሩ ከሚፈጠረው የትምህርት ጥራት ጉድለት በተጨማሪ ለተማሪዎች ትምህርት ማቋረጥ እንደምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

በቅርቡ በነበረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በርካታ የትምህርት ተቋማት ውድመት የደረሰበት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በአካባቢው የሚከሰተውን ተደጋጋሚ ድርቅ ጨምሮ በዚህ ወቅት የሕፃናት ምገባ ትኩረት የሚያስፈልገው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሦስት የተለያዩ አካላት አማካኝነት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ እየተካሄደ መኾኑን የነገሩን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኅላፊ አቶ ሰይፉ ሞገስ ናቸው፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ በዞኑ ከሚገኙ ሰባት ወረዳዎች ውስጥ በሁለት ወረዳዎች የተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ያካሂዳል ያሉት ኅላፊው በሦስት ወረዳዎች ኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ ተማሪዎችን እየመገበ ነው፡፡ በቀሪዎቹ ሁለት ወረዳዎች የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የተማሪዎችን ምገባ እንደሚያካሂዱ ኅላፊው ነግረውናል፡፡ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተደጋጋሚ በድርቅ እና በጦርነት የተጎዳ ነው ያሉት አቶ ሰይፉ የተማሪዎች ምገባ ዘላቂነት ባለው መንገድ ሊደገፍ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተማሪዎችን ምገባ ማካሄድ የጀመረው ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ነው ያሉን በኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሰፊው ብርሃኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ግን በ2013 ዓ.ም ነበር ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ አምስት ክልሎች የትምህርት ቤት ምገባ እያካሄደ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሦስት ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 56 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ እያካሄደ ነው ያሉት አቶ ሰፊው በአጠቃላይ ከ34 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ ተጠቃሚዎች ኾነዋል ብለዋል፡፡ ከምገባ አገልግሎት በተጨማሪም የሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ እና የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

“ልጆች ባሉበት ሁሉ ምግብ ይኑር” የሚለው መርህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሚዛን እየደፋ የመጣ የህጻናት መብት ጥበቃ ነው ያሉት ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጁ ኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡ የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎቱ በሀገሪቱ የሕግ ማዕቀፍ የተዘጋጀለት ግዴታ ኾኗል፤ ለስኬታማነቱ አብሮ መሥራት እና የተማሪዎችን መጻዒ ብሩህ ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ ለሁለት ቀናት የሚዘልቅ የትምህርት ቤት ምገባ አሥተዳደርን በተመለከተ የልምድ ልውውጥ እና ስልጠና በባሕር ዳር ከተማ ጀምሯል፡፡ እስከ ሰኔ 4/2015 ዓ.ም በሚቆየው ስልጠና እና የልምድ ልውውጥ መርሐ ግብር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና የአዲስ አበባ ምገባ ኤጀንሲ የሥራ ኅላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከመማር ማስተማር ባለፈ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የምርምር ሥራዎች እየተሠሩ ነው” የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት
Next articleበሀገሪቱ የሕግ የበላይነት ማስፈን የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልገሎት አስታወቀ፡፡