
ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ሰኔ 4 /1955 ዓ.ም በአሁኑ ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት ነበር የተመሠረተው። ዩኒቨርሲቲው የተመሠረተበትን 60ኛ ዓመት አስመልክቶ የቀድሞ ተማሪዎች የአልሙናይ ቀን ፎረም በኢንስቲትዩቱ ተካሂዷል። በፎረሙ የቀድሞ ተማሪዎች የሕይወት እና የሥራ ተሞክሯቻቸውን ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አካፍለዋል። ሰኔ 4/2015 ዓ.ም ደግሞ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ይካሄዳል።
የባሕርዳር ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ቢምረው ታምራት (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ከተመሠረተ ጀምሮ ከመማር ማስተማር ባለፈ በማኅበረሰብ አገልግሎት እና በምርምር ያከናወናቸውን ሥራዎች አንስተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በተለይም ደግሞ የተለያዩ ሶፎትዌሮችን በማበልጸግ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች መረጃ አያያዝ ሶፍትዌር በመፍጠር ለ21 ዩኒቨርሲቲዎች እንዲጠቀሙ አድርጓል። የመንጃ ፈቃድ ቁጥጥር ሥርዓትና የውኃ ቆጣሪ ክፍያ ሥርዓትን በመፍጠር አገልግሎት እንዲውል ማድረጉንም አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈ በዳንግላ አካባቢ የተቀናጀ የፀኃይ ኀይል መሥኖ ሥራ ሥርዓትን ጀርመን ሀገር ከሚገኘው ሙኒክ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የአካባቢው አርሶ አደሮች በዓመት ሦስት ጊዜ እንዲያለሙና የንጹህ መጠጥ ውኃ ማግኘት እንዲችሉ ተደርጓል። በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው አዳዲስ አሠራሮችን ለመሥራት ማቀዱን ገልጸዋል። የቀድሞ ተማሪዎችም የአልሙናይ ቀን መመሥረት ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ለሚያከናውነው ሥራ አቅም እንደሚፈጥር ነው ያነሱት።
የባሕርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት አምስተኛ ምሩቅ እና የአሉሙናይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጅነር ግዛቸው ሽፈራው እንዳሉት ደግሞ የተማሩበትን ዩኒቨርሲቲ እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ በተደራጀ መንገድ ለማገዝ የቀድሞ ተማሪዎች መሰባሰብ አስፈልጓል። ቤተ መጽሐፍት እና ትምህርት ቤት ግንባታ፣ በባሕርዳር ከተማ የብስክሌት ባሕል መፍጠርና የመሣሰሉ ሥራዎች በቀጣይ ትኩረት የተሠጣቸው ጉዳዮች መኾናቸውን አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!