“ለተማሪዎች ምግብ ማቅረብ ችሮታ ሳይኾን ግዴታ ነው” የትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እየሩስ መንግሥቴ

58

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በተመረጡ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ቀጣይነት ያለው የምገባ ፕሮግራም መዘርጋት እና ዘላቂ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ለመፍጠር የሁሉን አጋር አካላት ርብርብ እንደሚጠይቅ የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ ክልል አቀፍ የትምህርት ቤት ምገባ አሥተዳደር የልምድ ልውውጥ እና ስልጠና በባሕር ዳር አዘጋጅቷል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የህጻናትን መጻዒ እጣ ፋንታ ባልተጠበቀ መንገድ በአሉታዊ ገጽታ ሲቀርጹት ማየት የተለመደ ነው፡፡ ሀገሪቱ ወቅት እያየ በየወቅቱ የሚፈትናት ድርቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናት በልጅነት ዘመናቸው ማግኘት የሚገባቸውን ሥነ-ምግብ እንዳያገኙ አድርጓል፡፡ ይህም በገሃድ ከሚስተዋለው አካላዊ ተፅዕኖ በላይ በሥነ-ልቦና ደረጃ በቀላሉ ታክሞ የማይድን ሥብራትን ሲፈጥር ተስተውሏል ይላሉ፡፡

በሀገሪቱ በተለይም በአማራ ክልል የተከሰቱት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ የአምበጣ መንጋ መከሰት እና በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው ድርቅ በህጻናት ምግባ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳሳደሩ ይነገራል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከመንግሥት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ቀረጻ ባሻገር የሁሉንም አጋር አካላት የጋራ ተሳትፎ ይጠይቃል ያሉት የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ ናቸው፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ውስብስብ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ክልሉን በከፍተኛ ኹኔታ ፈትነውታል ያሉት ወይዘሮ አበራሽ ከፍተኛ ተፅዕኖ ካረፈባቸው ተቋማት መካከል የትምህርት ሴክተሩ ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡ ላለፉት ዓመታት በነበረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በርካታ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል ያሉት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ አሁናዊን የበርካታ ትምህርት ቤቶች ገጽታ በሚገባ ላስተዋለ ለመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ አለመኾናቸውን ይረዳል ነው ያሉት፡፡

የበርካታ ሀገራት የእድገት ሚስጥር ትውልድ ግንባታ ላይ መጠነ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሳቸው ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኅላፊ ወይዘሮ እየሩስ መንግሥቴ ናቸው፡፡ ባለፉት ጊዜያት የትምህርት ሥርዓታችን ዘርፈ ብዙ ስብራቶች ገጥመውት ትውልድ ግንባታ ላይ ክፍተቶች ተስተውለዋል ያሉት ምክትል ኅላፊዋ ችግሩ ለአሁናዊ ፈተናዎቻችን እንደዳረገን ማየት ይቻላልም ነው ያሉት፡፡

ወይዘሮ እየሩስ የትምህርት ቤቶች ደረጃ አለመሻሻል፣ የመምህራን ልማት መርኃ ግብር ክፍተት እና ሌሎችም ተያያዥ ጉድለቶች ለትምህርት ሥርዓቱ ስብራት እንደምክንያት ሊነሱ እንደሚችሉ አንስተው የተማሪዎች የምገባ ሥርዓት አለመኖር ግን ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡ “ለተማሪዎች ምግብ ማቅረብ ችሮታ ሳይኾን ግዴታ ነው” ያሉት ምክትል ቢሮ ኅላፊዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት በስፋት እየተተገበረ እንደኾነ አንስተዋል፡፡

የተማሪዎች ምገባ መንግሥት እና የተወሰኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሚያደርጉት ጥረት ብቻ አይሳካም፡፡ በመኾኑም ባለሃብቶች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ ለጋሽ ድርጅቶች እና ማኀበረሰቡ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ በተማሪዎች ምገባ ኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ ላለፉት ዓመታት እያደረገ ያለውን ጥረት ያደነቁት ወይዘሮ እየሩስ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ ክልል አቀፍ የትምህርት ቤት ምገባ አሥተዳደር የልምድ ልውውጥ እና ስልጠና በባሕር ዳር እያካሄደ ነው፡፡ በልምድ ልውውጡ የአዲስ አበባ ምገባ ኤጀንሲን ጨምሮ ከዞን፣ ከወረዳ እና ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ እንግዶች ተሳታፊዎች ኾነዋል፡፡ በልምድ ልውውጡ የኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሼቲቭ ያለፉት ዓመታት ጉዞ እና የቀጣይ ጊዜያት መርኃ ግብሮች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየትላንት ኩራቶች የዛሬ መከታዎች የላቀ ተልዕኮ ይዘው ተመርቀዋል።
Next article“የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም መቆም ቀዳሚው እሴቱ ነው” የመከላከያ ሚኒስቴር