
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከቀድሞው የአማራ ልዩ ኀይል ወደ አማራ ፖሊስ በምርጫቸው ገብተው ተጨማሪ ስልጠናዎችን አጠናቀው በጥሩ ብርሃን በሠረታዊ ፖሊስ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ተመርቀዋል።
በምርቃቱ ላይ የተገኙት የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደጀኔ ልመንህ፤ ሴረኞች ሀገርን ከመፍረስ ዋጋ የከፈለው የአማራ ልዩ ኀይል ክብሩን በማይመጥን መልኩ እንዲበተን እየጣሩ ነበር ብለዋል። ይሁን እንጅ ቀደም ሲል በአማራ ልዩ ኀይል አባልነት ታሪክ የሠሩ አባላት ዛሬ ደግሞ ዘመኑ የደረሰበትን ረቂቅ የወንጀል አፈጻጸም ቀድሞ በመረዳትና በመተንተን መከላከል የሚችሉ ዘመናዊ ፖሊሶች ኾነዋል ብለዋል።
ተመራቂዎች ወደተመደቡበት አካባቢ በመሄድ ጥበብ የተሞላበት ፓሊሳዊ ተግባራቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። መላው የአማራ ሕዝብም ከጀግኖች ፖሊሶቻቸን ጎን በመኾን ሰላሙን ማረጋገጥ እና በሙሉ ልብ ወደ ልማት መግባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ኮሚሽነሩ ተመራቂዎች የተመደቡበትን አካባቢ ሁሉ ሰላም በማድረግ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት የፈጸሙትን አኩሪ ታሪክ ማስቀጠል እንዲችሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈው የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።
ሀገር ሰላም እንድትሆን ታሪክ የማይዘነጋው ተግባር የፈጸሙ የቀድሞ የአማራ ልዩ ኀይል አባላት በራሳቸው ፈቃድ እና ምርጫ ወደ አማራ ፖሊስ ኮሌጅ ገብተው ተጨማሪ ክህሎት ይዘው ተመርቀዋል ብለዋል።
ማኅበረሰባችን ሙሉ ሰላሙ ተረጋግጦ በሙሉ ልቡ ወደ ልማቱ እንዲገባ ዛሬ የተመረቁ የፖሊስ አባላት ለፈተናዎች ሁሉ ብልሃት የተሞላበት መፍትሄ በማበጀት ፓሊሳዊ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ተመራቂዎች በበኩላቸው የክልል ልዩ ኀይሎችን መልሶ የማደራጀት ተግባር ተቀብለው በምርጫቸው መሰረት ወደ አማራ ፖሊስ መቀላቀላቸውን ተናግረዋል። በፖሊስ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ በነበራቸው ቆይታ ተጨማሪ ክህሎቶችን ማግኘታቸውን ገልጸው በተመደቡበት አካባቢ ሁሉ በመሄድ ለሀገር እና ለሕዝብ ሰላም እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!