የዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ባሕር ዳር ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጠባቂውን ጨዋታ ዛሬ ያደርጋሉ።

239

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ተከታዩ ባሕር ዳር ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ በዛሬው ዕለት በጉጉት ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።

ጨዋታው በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ግንቦት 18/2015 መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በከባድ ዝናብ ምክንያት ሜዳው ማጫወት ባለመቻሉ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞ የቆየ ነው።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የውድድር እና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ጨዋታው በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስታዲየም እንዲደረግ መወሰኑ ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት የሁለቱ ክለቦች ወሳኝ ጨዋታ ዛሬ ይከናወናል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ58 ነጥብ 1ኛ ሲሆን ባሕር ዳር ከነማ በ53 ነጥብ 2ኛ ደረጃን ይዟል።

በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚሰለጥነው ቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ አሁን በፕሪሚየር ሊጉ ካደረጋቸው 26 ጨዋታዎች 17ቱን ሲያሸንፍ 2 ጊዜ ተሸንፎ፤ 7 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

በ26ቱ ጨዋታዎች ፈረሰኞቹ 48 ግብ ሲያስቆጥሩ 17 ጎሎችን አስተናግደዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች በሶስቱ አሸንፎ በአንድ ተሸንፎ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባሕር ዳር ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 26 ጨዋታዎች 15ቱን ሲያሸንፍ በሶስቱ ተሸንፎ፤ በ8ቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

የጣና ሞገዶቹ በ26ቱ ጨዋታዎች 47 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ 24 ግቦችን አስተናግደዋል።

ባህር ዳር ከተማ ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሶስቱን አሸንፎ አንዱን ተሸንፎ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቢቡኝ ወረዳ የወይን ውኃ ታዳጊ ከተማን የውኃ ችግር ለመፍታት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ገለጸ።
Next articleየትላንት ኩራቶች የዛሬ መከታዎች የላቀ ተልዕኮ ይዘው ተመርቀዋል።