የቢቡኝ ወረዳ የወይን ውኃ ታዳጊ ከተማን የውኃ ችግር ለመፍታት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ገለጸ።

61

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምስራቅ ጎጃም ዞን ስር የምትገኘውን የቢቡኝ ወረዳ የወይን ውኃ ታዳጊ ከተመን የውኃ ችግር ለመፍታት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ገልጿል።

በ1950 ዓ.ም እንደተቆረቆረች ይነገርላታል በምስራቅ ጎጃም ዞን ስር የምትገኘው የቢቡኝ ወረዳ የወይን ውኃ ታዳጊ ከተማ። የዚች ከተማ ነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ በሄደ ቁጥር የመጠጥ ውኃ ችግሩም እያደገ መጥቷል።የአሚኮ ጋዜጠኞች ቡድንም በወይን ውኃ ታዳጊ ከተማ ተገኝቶ ነዋሪዎች በውኃ እጦት ምክንያት የሚያጋጥማቸውን ችግር ተመልክቷል። ወይን ውኃ ከውኃ ማማው ጮቄ ግርጌ ተቀምጣ የውኃ ችግር እያጋጠማት ያለች ከተማ ናት።

መላዕከ ብስራት መሪጌታ ጥበቡ አንተነህ የወይን ውኃ ከተማን የመጠጥ ውኃ ችግር እስከ ክልል ድረስ በማሳወቅ መፍትሄ ከሚያፈላልጉ ነዋሪዎች ውስጥ አንዱ ናቸው። ነዋሪው የከተማዋን የውኃ ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠሩ ስለመኾናቸው ነግረውናል።

መሪጌታ ጥበቡ የከተማዋ የመጠጥ ውኃ ችግር እንዲፈታ ጥያቄ እየቀረበ ያለው ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ነው ብለዋል። እንደ መፍትሄ የተጀማመሩ ሥራዎች መኖራቸውን የነገሩን ነዋሪው አሁንም ግን የክልሉ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ለችግሩ ትኩረት እና መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ወይዘሮ አያል ክንዴ የወንዝ ውኃ ሲቀዱ ነው ያገኘናቸው። “ልብስ የምናጥበው እዚሁ፣ የመጠጥ ውኃ የምንቀዳውም አዚሁ ነው” ብለዋል።”የመጠጥ ውኃ ችግራችን ተፈትቶ እፎይ ማለት እንፈልጋለን” ሲሉም ያላቸውን ፍላጎት ወይዘሮ አያል ነግረውናል።

ስለጉዳዩ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ተስፉየ አባቡ በወይን ውኃ ታዳጊ ከተማ ውስጥ የገጠመውን የውኃ ችግር ቢሯቸውም የሚገነዘበው ስለመኾኑ ተናግረዋል። ቢሮው ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

አቶ ተስፋየ የወይን ውኃ ከተማን የመጠጥ ውኃ ግንባታ ጥያቄ ለመመለስ የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ተጀምሮ ነበር ብለዋል። ይሁን እንጅ አካባቢው ላይ በቂ የከርሰ ምድር ውኃ ሊገኝ አልቻለም። በዚህ ምክንያት የከርሰ ምድር ውኃ ቁፋሮ ፕሮጀክቱ ቢቋረጥም ሌላ አማራጮችን በመፈለግ የከተማዋን የውኃ ችግር ለመፍታት እየተሠራ ስለመኾኑ አቶ ተስፋየ ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተወሰደው አማራጭ በከተማዋ አቅራቢያ የሚገኘውን ወንዝ በመጥለፍ አጣርቶ ለመጠጥ ማዋል ነው። በክልሉ አብዛኛው አካባቢዎች በጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ የከርሰ ምድር ውኃን የመጠቀም እንጅ የገጸ ምድር ውኃን አጣርቶ የመጠቀም ልምድ ብዙም የካበተ እንዳልኾነ አቶ ተስፉየ አንስተዋል። የከርሰ ምድር ውኃ ሥራዎች ላይ ልምድ ያላቸው ተቋራጮች በክልሉ ባለመኖራቸው ዘርፋን አስቸጋሪ አድርጎታልም ነው ያሉት።

የወይን ውኃ ከተማ የገጸ ምድር ውኃ ሥራን ለማስጀመርም ልምድ ያለው ተቋራጭ በመጥፋቱ እንደተጓተተ አቶ ተስፋየ ገልጸዋል። ቢሮው የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በቅርብ ቀን ሀገር አቀፍ ጨረታ አውጥቶ ተቋራጮችን ወደ ቦታው እንደሚያስገባ ተናግረዋል።

በዚህ መልኩ ዘላቂ መፍትሄ እስከሚገኝ ድረስ ለማኅበረሰቡ የውኃ ችግር እፎይታን የሚሰጡ መለስተኛ ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል። መለስተኛ ጥልቅ ጉድጓዶችን በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ በቅርቡ የቱቦ ማጓጓዝ ሥራ እንደሚጀመር ምክትል ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። ወዲያውኑ የገጠማ ሥራ ተከናውኖ ጊዜያዊ መፍትሄ ይሰጣልም ብለዋል።

የውኃ ጉዳይ ጊዜ አይሰጥምና በቅርብ ይፈጸማሉ ተብለው በቢሮው ቃል የተገቡ ሥራዎችን ስለመፈጸማቸው አሚኮ በክትትል ዘገባው በቀጣይነት የሚዳስስ ይኾናል።

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ “ፈር ቀዳጅ ሴት” እውቅና ተበረከተላቸው።
Next articleየዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ባሕር ዳር ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጠባቂውን ጨዋታ ዛሬ ያደርጋሉ።