ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ “ፈር ቀዳጅ ሴት” እውቅና ተበረከተላቸው።

73

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ “ፈር ቀዳጅ ሴት” እውቅና ተበረከተላቸው።

ፕሬዚዳንቷ በቤልጂየም ፓርላማ በተካሄደውና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች አመራር ሴቶች በተገኙበት የሴት ፖለቲካ መሪዎች ድርጅት ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ነው እውቅናው የተበረከተላቸው።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን ጨምሮ ከዚህ በፊት በተመድ ውስጥ በተለያዩ የስራ ዘርፎች በነበራቸው ከፍተኛ የኃላፊነትና የመሪነት ቦታዎች ፈር ቀዳጅ በመሆናቸውም ጭምር ያገኙት እውቅና መሆኑ ተገልጿል።

ፕሬዚዳንቷ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ሽልማቱ ለብርቱዎቹ ሴቶች፣ በመጠለያ ጣቢያዎች ላሉት፣ ተማርከው ሕክምና ላይ ሆነው ሲጎበኟቸው የመማር ጉጉት እንዳላቸው ለነገሯቸው፣ ብቻቸውን ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነት ለተጣለባቸው እና ተስፋ ለሚሰጡን ባለ ተሰጥኦ የሀገሬ ሴቶች ይሁንልኝ ብለዋል።

በዋዜማው ፕሬዚዳንት ሣኅለ ወርቅ በአውሮፓ ፓርላማ “ ውክልና ወሳኝ ነው “ በሚል ርዕስ በተጀመረው በዚህ ጉባኤ ላይ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም ሴቶች በሰላም እና ደህንነት ዙሪያ ስለሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች እና የሴቶች ውክልና በቁጥር ብቻ መተርጎም እንደሌለበት መናገራቸውን የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

10ኛው የሴት ፖለቲካ መሪዎች ድርጅት ዓመታዊ ጉባዔ በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ እና በቤልጂየም ፌዴራል ፓርላማ “ውክልና ወሳኝ ነው” በሚል መሪ ቃል በጋራ ተካሂዷል።

የዘንድሮው ዝግጅት አስተናጋጅ ሀገር ቤልጂየም በአሁኑ ጊዜ በሴቶች አፈ ጉባኤዎች የሚመሩ ሁለት ምክር ቤቶች አሏት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር 105 የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የአስተዳደሩ የትምህርት መምሪያ አስታወቀ።
Next articleየቢቡኝ ወረዳ የወይን ውኃ ታዳጊ ከተማን የውኃ ችግር ለመፍታት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ገለጸ።