በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር 105 የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የአስተዳደሩ የትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

65

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 03/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይፉ ሞገስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በብሄረሰብ አስተዳደሩ በርካታ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች በመሆናቸው ለትምህርት ጥራት መጓደል መንስኤ ሆነዋል።

በተለይም በሰሃላና ዝቋላ ወረዳዎች በ11 የዳስና የዛፍ ጥላ ስር ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በብሄረሰብ አስተዳደሩ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለመቀየርና የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የመማሪያ ክፍሎቹ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከግንባታዎቹ ውስጥ ከ30 በላይ የዳስ ጥላ ስር መማሪያ ክፍሎች ደረጃውን ወደ ጠበቀ ትምህርት ቤት መቀየር እንደሚገኝበት ሃላፊው ጠቁመዋል።

እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት በደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች 75 የመማሪያ ክፍሎች በመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም መርሐ ግብር አማካኝነት ግንባታቸው እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

ግንባታው በትምህርት ሚኒስቴር፣ ከተለያዩ ተቋማት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍና በኅብረተሰብ ተሳትፎ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የቃርሸዋ ትምህርት ቤት መምህር ፋንታ ጥጋቡ በዳስ በተሰሩ የመማሪያ ክፍሎች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች የጤና ችግር እየገጠማቸው ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተል ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል።

ዘንድሮ ግን አራት የመማሪያ ክፍሎች ግንባታቸው ተጠናቆ የመማር ማስተማር ሥራ በመጀመራቸው ለተማሪዎችም ሆነ ለመምህራን ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል።

መማሪያ ክፍሎቹ በዘመናዊ መልኩ እየተገነቡ በመሆናቸው ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሚገባ ተከታትለው የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጉጉት ሲጠበቅ የቆየው የባሕር ዳር ከነማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ጨዋታ ዛሬ ይካሔዳል።
Next articleፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ “ፈር ቀዳጅ ሴት” እውቅና ተበረከተላቸው።