“የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል”

66

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) እርግጥ ነው በዚያ አካባቢ ያ መራር የኾነ የጨለማ ጊዜ ዳግም ላይመለስ አልፏል፡፡ ከሞት የከፋ ሕይዎትን፤ ከስደት የከፋ ባርነትን ዳግም ለመሸከም የሚችል ትከሻ አሁን ላይ ፈጽሞ አይስተዋልም፡፡ ለሰላም ያላቸው ቀናዒነት ደም አፋሳሽ ጦርነት የቱን ያክል እንደሰለቻቸው ቢያሳብቅም ነጻነታቸውን ግን ለድርድር አያቀርቡም፡፡ አሁን የሚያጣጥሙትን ነጻነት ለማምጣት ለማመን የሚከብድ የብዙ ዘመን ዋጋ ከፍለውበታል፡፡

ለማንነታቸው መከበር ሲሉ እልፎች ደማቸው ደመ-ከልብ ኾኖ በግፈኞች እጅ ፈስሷል፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃን በግፍ ተጨፍጭፈው በጅምላ መቃብር ተቀብረዋል፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖች ርስታቸው ተነጥቆ እና ማንነታቸው ተጨፍልቆ ከሀገር ሀገር በስደት ተንከራትተዋል፡፡ በእነዚያ አሰቃቂ ዓመታት የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የሰቲት ሁመራ እና የራያ አማራዎች ከሞቱት በላይ ካሉት በታች ኾነው የማያልፍ የሚመስለውን የግፍ ጊዜ እና የጨለማ ዘመንን አሳልፈዋል፡፡

የሚገርመው ግን ከሕይዎት እና ሃብት በላይ ማንነታቸውን፤ ከርስት እና መሬት በላይ ነጻነታቸውን አጥብቀው የሚፈልጉት አማራዎች መራር የሚባለውን ትግል በጽናት ማለፋቸው ነው፡፡ ራሳቸውን ግፈኞቹን እስኪገርማቸው ድረስ ልጆቿን በግፍ የተነጠቀች እናት በድፍረት እና በጽናት ከግፈኞቹ ፊት ለፊት ቆማ “አማራ ነን” እንዳለቻቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ወኔ ከማንነት በላይ የኾነ ጀግንነትን ይጠይቃል፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ነባር እሴት ባፈነገጠ ነውር አኳኋን በተለያየ አጋጣሚ “እኛ ከወልቃይት እና ራያ የምንፈልገው መሬቱን እና ሴቱን ነው” ሲሏቸውም መሬቱም የአማራ ሴቶቹም አማራ ናቸው ብለው በድፍረት ነግረዋቸዋል፡፡

ወንዶቹ ከፋኝ ብለው ተደራጅተው ጤዛ እየላሱ እና ድንጋይ እየተንተራሱ እልፍ ሌሊቶችን በተጋድሎ አሳልፈዋል፡፡ የእርሻ መሬቶቻቸውን ተነጥቀው፤ በሬዎቻቸው ተነድተው መሣሪያቸውን ብቻ እንደወንድም አምነው ግፈኞችን እስከ ህቅታ ድረስ ተፋልመዋል፡፡ ወቅቱ በሀገሪቱ የነበረው መንግሥት በተለያዩ ፈተናዎች የተወጠረበት እና ኢትዮጵያዊያንም ከውጭ ጠላት ጋር አንገት ለአንገት የሚተናነቁበት ጊዜ ስለነበር እንደ ፍልፈል መሬት ምሰው ለገቡት ሽፍቶች ብዙም ትኩረት የሰጠ አለመኖሩ እግራቸው ከዳር አልፎ መሃል ሀገር እንዲረግጥ እረዳቸው፡፡ በጊዜው የወልቃይት፣ ጠለምት እና የራያ ሕዝብ ህወሐትን እንደመታገሉ አጋዥ አግኝቶ ቢኾን ኖሮ ከተከዜ መሻገር ቀርቶ ከተከዜ ወዲያ ማዶም ስለመኖራቸው እርግጠኛ ባልተኾነ ነበር፡፡ ዳሩ ክፉ ቀን ለክፉ አሳልፎ ሰጣቸውና የከፉ የሚባሉ ጊዜያትን ለማሳለፍ ተገደዱ፡፡

“በግፍ የበለጸገ በግፍ ይደኸያል” እንዳለ መጽሐፍ ፤ የግፍ ጽዋ ሞልቶ በመፍሰሱ ማንነታቸውን በግፍ የተነጠቁ አማራዎች ወደ ቀደመ ማንነታቸው የሚመለሱበት ጊዜ በዚህ ትውልድ ዘመን ተከሰተ ያሉን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ የኾኑት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ ናቸው፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ወረራ እና መዋቅራዊ ዘር ማጥፋት ላይ የተሰማራው የጥናት ቡድን መሪ ናቸው፡፡ ከሽፍትነት ተነስቶ ትጥቅ ትግል ከዚያም ሀገር እስከ መምራት የደረሰ እድል ያገኘው ህወሐት በአካባቢው ሕዝብ ያደረሰው ዘርን መሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያልታየ ነበር ይላሉ፡፡

አካባቢውን በኃይል የተቆጣጠሩት “የታላቋ ትግራይ” መሥራቾች አማራዎችን ከርስቶቻቸው በማጽዳት ከመሃል ትግራይ ሳይቀር ዜጎቻቸውን እያመጡ ያሰፍሩ ነበር፡፡ ገና ደደቢት በርሃ ሳይገቡ በስሁት ትርክት እና በተሳሳተ ስሌት አማራ ጠላት ነው ብለው በማኒፌስቶ እስከ ማውጣት የደረሱት የህወሐት ሰዎች አቅማቸውን እና ኹኔታውን እያዩ ተስፋፊነታቸውን ያጠናክሩ ነበር፡፡ ህወሐት በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ባወጣው ማኒፌስቶ “በምዕራብ በኩል እስከ ሱዳን ድንበር ለመድረስ ወልቃይትን እና ሰቲት ሁመራን፤ በወሎ በኩል ደግሞ አልውኋ ምላሽ ድረስ ለመስፋፋት አልመው ተነሱ” ይሉናል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ በወቅቱ የነበረው የህወሐት የመሬት ወረራ እና መስፋፋት ከሕግም ከሞራልም ያፈነገጠ እንደነበር ማሳያዎችን ጠቅሰው ያነሳሉ፡፡ የመጀመሪያው ገና ሲነሱ ወልቃይት እና ሰቲት ሁመራን በመያዝ ከሱዳን ጋር ለመገናኘት የነበራቸውን ፍላጎት ካሳኩ በኋላ አቅም እየፈጠሩ ሲመጡ ጠገዴንም አጠቃለሉ ይሉናል፡፡ ጠገዴ በመጨረሻው የወረራ ጊዜ ወደ ትግራይ የተካተተ አካባቢ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በሂደትም መተማ እና ቋራን በማካተት “ታላቋን ትግራይ” እስከ ቤንሻንጉል ጉምዝ ድረስ ለማስፋት ካርታ ሠርተው በመማሪያ መጽሐፍት ላይ አውጥተው እስከማስተማር ደርሰው ነበር ይላሉ፡፡

አሁን ያለውን መንግሥት ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በአካባቢው የተፈጸመውን ግፍ ጠንቅቀው ያውቃሉ የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ፤ በሕገ-መንግሥት ያልሄደን አካባቢ በሕገ-መንግሥት ይመለስ ማለት በራሱ ካለፈው ጥፋት ያለመማር አባዜ ነው ይላሉ፡፡ የአካባቢው ሕዝብ ጥያቄ ለሁሉም ግልጽ ነው፤ ለዘመናት የዘለቀው ጥያቄ ማንነታችን ይከበር፣ ባሕላችን ይጠበቅ እና በቋንቋችን እንገልገል ነው፡፡ ይህንን ፍትሃዊ ጥያቄ ለመመለስ ሦስት ዓመታትን ማስቆጠር በራሱ በአካባቢው ላይ ድጋሚ ጥቃት እንደመሰንዘር ይቆጠራል ብለዋል፡፡

የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ፣ ጠለምት እና ራያ ሕዝብ የማንነት ጉዳይ በሕግ ይረጋገጥ ቢባል እንኳን ከሦስት ዓመታት በላይ ያለበጀት ማቆየት “ኢትዮጵያዊ አይደላችሁም፤ አናውቃችሁም” እንደማለት ይቆጠራል ብለዋል፡፡ የአካባቢው ሕዝብ ለዘመናት ተገፍቶ እና ተለይቶ የቆየ ሕዝብ በመኾኑ ከነጻነቱ ባሻገር ላሉ ነገሮች ሁሉ እስካሁን ትኩረት ሳይሰጥ ቆይቷል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አሁን ግን ግልጽ ጥያቄ ለሚመለከተው አካል አቅርቧል ነው ያሉት፡፡

ምንም እንኳን የጦርነቱ ነጋሪት ጎሳሚዎች እና ቀስቃሾች ራሳቸው የህወሐት ሰዎች ቢኾኑም በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት ለተጎዳው የትግራይ ሕዝብ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ መንግስት ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በጨለማ ውስጥ ላለፈ ሕዝብ ትኩረት መንፈግ አሁናዊውን መንግሥት ከታሪክ ተወቃሽነት እና ከሕግ ተጠያቂነት የሚያድን አይደለም ይላሉ፡፡

ከሰሞኑ በተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች የተካሄዱት ሕዝባዊ ሰልፎችም ማንነታችን ይከበር እና እንደ ኢትዮጵያዊ ታይተን በጀት ይመደብልን የሚል መልዕክት አለው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ፤ በተለይ ደግሞ ሠላምን አጥብቀን እንሻለን፤ ነገር ግን ለነጻነታችን እና ለማንነታችን የማንከፍለው ዋጋ የለም የሚለው መልዕክት መንግሥት ጉዳዩን በአፋጣኝ ተመልክቶ እልባት እንዲሠጥ የሚያሳስብ ቁልፍ ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡ “የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል” እንደሚባለው ሁሉ የአማራ ክልል እና የፌደራል መንግሥት የሚጠበቅባቸውን ባለመሥራታቸው ከሰብዓዊነት ይልቅ ፖለቲካ ለሚያስጨንቃቸው የውጭ ኃይሎች መግቢያ ቀዳዳ እያመቻቸ ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጥራሪ ወንዝ ድልድይ ጥገና የፊታችን ማክሰኞ እንደሚጀመር የዋግኸምራ ብሄረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡
Next articleአትሌት ለሜቻ ግርማ የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል የዓለም ክብረ ወሰን ሰበረ።