የጥራሪ ወንዝ ድልድይ ጥገና የፊታችን ማክሰኞ እንደሚጀመር የዋግኸምራ ብሄረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡

55

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የጻግብጅ ወረዳን ከሰቆጣ ጋር የሚያገናኘውን ብቸኛ ድልድይ ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መኾኑን የዋግኸምራ ብሄረሰብ አሥተዳደር አስታውቋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ጉዳት ከደረሰባቸው ትላልቅ ድልድዮች መካከል ሰቆጣና ጻግብጅን የሚያገናኘው የጥራሪ ድልድይ አንዱ ነው፡፡

ይህ ድልድይ ተጠግኖ ወደ አገልግሎት አለመመለሱ በአካባቢው ላይ ተጽኖ ማሳደሩን ከዚህ በፊት አሚኮ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

የዋግኸምራ ብሄረሰብ አሥተዳደር የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ኀላፊ ከፍያለው ደባሽ፤ የጥራሪ ድልድይ የጻግብጅ ወረዳን ከሰቆጣ ጋር የሚያገናኝ ብቸኛው ድልድይ ስለመኾኑ ተናግረዋል።

ኀላፊው ድልድዩ ባለመሠራቱ የበልግ ወቅትን መግባት ተከትሎ በጣለው ዝናብ ማኅበረሰቡን መልሶ ለማቋቋም፣ ድጋፎችን ለማቅረብ፣ የወደሙ የመንግሥት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት፣ የንግድ ሥራዎችን ለማከናዎንና የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር ፈተና ኾኖ ቆይቷል ነው ያሉት።

ይሁን እንጅ ችግሩን ለመፍታ በመንግሥት በኩል ጥረት ሲደረግም ቆይቷል ብለዋል፡፡

አቶ ከፍያለው ይህን ብቸኛ ድልድይ ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት የተገጣጣሚ የብረት ድልድይ ወደ ዋግኸምራ ብሄረሰብ አሥተዳደር እየገባ መኾኑን ገልጸው የፊታችን ማክሰኞ ሥራው ይጀመራል ብለዋል፡፡

ሥራው 8 ቀናት እንደሚፈጅ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም ኀላፊው ነግረውናል፡፡

የድልድዩ ሥራ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ሲመለስ የአካባቢውን ችግሮች እንደሚፈታም ነው አቶ ከፍያለው ያብራሩት፡፡

ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዓለም አቀፉ ‘የቤተሰብ ሬሚታንስ መላኪያ ቀን’ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ይከበራል” የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት
Next article“የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል”