
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 19/2012ዓ.ም (አብመድ) በአዊ ብሔረሰብ አስተዳድር ዳንግላ ወረዳ የሚኖሩ ወጣቶች ንብ በማነብ ሥራ ተሰማርተዋል፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅትም በወረዳው የሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ላይ ቅኝት አድርጓል፡፡ በወረዳው ተደራጅተው ንብ የማነብ ሥራ ላይ ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል ፀሐይነህ ገኔ የዳንግላ ወረዳ ለንብ ማነብ ተስማሚ የአየር ንብረት ስላለው በንብ ማነብ ሥራ መሠማራታቸውን ተናግሯል፡፡ ከ20 በላይ ባሕላዊ እና ዘመናዊ ቀፎም አላቸው፡፡
የንብ ማነብ ሥራው ጠቃሚ የሚያደርገው ከሌላ ሥራ ጋር በተጓዳኝ ለመሥራት ምቹ የሥራ ዘርፍ በመሆኑ እንደሆነ ነው ወጣቱ የጠቆመው፡፡ በዚህ ዓመት በማኅበሩ እስከ 50 ሺህ ብር ለማግኘት እቅድ እንዳላቸው የተናረው ፀይሐይነህ ባለፈው ዓመት በዚሁ ዘርፍ ባገኙት ገቢ የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን ሕይወት መምራት መቻላቸውን ተናግሯል፡፡ ይህም ሆኖ ንብ ለማነብ የሚገለገሉበት ቁሳቁስ እጥረት እንዳጋጠማቸው አስረድቷል፡፡
ሌላው በዳንግላ ወረዳ ያነጋገርነው ወጣት ሰዋገኝ ይስማው “ንብ ማነብ ከዚህ በፊት በባሕላዊ መንገድ ሲሠራ ስለነበር ብዙም ተጠቃሚ አላደረገንም፤ አሁን ግን ስልጠና ወስደን በዘመናዊ ቀፎ ንብ የማነብ ሥራ እየሠራን በመሆኑ መለወጥ ችለናል” ብሏል፡፡ ንቦች የሚፈለገውን ምርት እንዲሰጡ ደግሞ በአቅራቢያቸው አበባ፣ ውኃ እና ዱቄት እንዲኖር በማድረግ ለንብ ማነቡ ሥራ ተገቢውን እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ነው ወጣቱ የተናገረው፡፡
“ንቦችን ጉንዳንና ሌላም ተባይ እንዳያባርራቸው በየጊዜው በንቃት ጥበቃ እናደርጋለን፡፡ ከንብ ማነብ ጎን ለጎን የእርሻ፣ የከብት ማድለብ እና ሌሎችም ሥራዎችን ለመሥራት ያስችለናል፡፡ መንግሥት ወጣቱን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንደሚያደራጀው ሁሉ ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል ሊያደርግ ይገባል” ብሏል፡፡
የዳንግላ ወረዳ እንስሳት ሀብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን መስፍን ደግሞ ወጣቶች በእንስሳት ሀብት ልማት ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተጠሪ ፅሕፈት ቤቱ በእቅድ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ወረዳው “በዳንግላ በግ” እርባታ እና በማር ምርት የተሻለ በመሆኑ በሰፊው ወጣቶችን በማደራጀት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡
በወረዳው በ2011/12 የምርት ዘመን 307 ቶን የማር ምርት እንደሚገኝም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በከብት ማድለብ፣ በንብ ማነብ እና በሌሎች የግብርና ሥራዎች ላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ስልጠና ተሰጥቶ ወደ ሥራ የተገባ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅፋት የሚሆኑትን ጉዳዮች ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር በመነጋጋር መፍትሔ እንደሚሰጥም አስታውቀዋል፡፡
በወረዳው 15 ሺህ 469 የንብ መንጋ እንደሚገኝ እና የአየር ንብረቱም ለንብ ማነብ ተስማሚ ከሆኑ አካባቢዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን ነው ጽሕፈት ቤቱ ያስታወቀው፡፡
በወረዳው ከ800 በላይ ወጣቶች በዘርፉ መሠማራታቸው እና ውጤታማ መሆናቸውን ከወረዳው እንስሳት ሀብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው