“ዓለም አቀፉ ‘የቤተሰብ ሬሚታንስ መላኪያ ቀን’ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ይከበራል” የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት

133

ባሕር ዳር: ሰኔ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፉ ‘የቤተሰብ ሬሚታንስ መላኪያ ቀን’ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚከበር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታውቋል።

አገልግሎቱ ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት /ጂ.አይ.ዜድ/ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ቀኑን በልዩ ልዩ መርኃ ግብሮች ለማክበር ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

በዕለቱ ለቤተሰብ የሚላክ ሬሚታንስ ድህነትን በመቀነስ የቤተሰቦችን ሕይወት ከማሻሻል አንጻር የሚያበረክተው አስተዋጽኦን እንዲሁም በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሬሚታንስን ለመላክ እንደ ሀገር ያሉን አማራጮች እና ዕድሎችን የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

ለቤተሰብ የሚላክ ሬሚታንስን ፍሰት እና አስተዋጽኦውን ከማሳደግ አንጻር ያሉ ተግዳሮቶች የሚፈቱበት አቅጣጫም ይመላከታል።

ከሀገራቸው ውጪ በሚኖሩ ሰዎች ከሚላከው ገንዘብ ውስጥ ግማሽ የሚሆነው በድህነት በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ተጎዱ የገጠር አካባቢዎች የሚሄድ በመሆኑ የሰዎችን ሕይወት በመለወጥ ረገድ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

“በመሆኑም ዕለቱን ስንዘክር የሚላከው ገንዘብ የቤተሰቦችን፣ የማኅበረሰቦችን እና የሀገርን ነባራዊ ሁኔታ ከመቀየር አንጻር ያለው ሚና ላይ ግንዛቤ መፍጠር እና የሚላከው ገንዘብ ይበልጥ ውጤታማ በሆኑ ተግባራት ላይ የሚውልበትን ሁኔታ በማመላከት ሊሆን ይገባል” ሲል የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስገንዝቧል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ ሬሚታንስ ከሚቀበሉ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን የገለጸው አገልግሎቱ፣ ሀገሪቱ ውጪ ከሚኖሩ ዜጎቿ በዓመት በአማካኝ ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ሬሚታንስ እንደምታገኝ ጠቁሟል።

በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ 626 ቢሊዮን ዶላር በዕድገታቸው ወደ ኋላ ቀርተዋል ወደ ሚባሉ ሀገራት ተልኳል ። በውጭ ሀገር የሚኖሩ ሰዎች ወደ ሀገር ቤት በአማካኝ ከ200 እስከ 300 ዶላር በወር እንደሚልኩም ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእየተበራከተ ያለውን በጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆችን ቁጥር በመደጋገፍ መቀነስ ያስፈልጋል ተባለ።
Next articleየጥራሪ ወንዝ ድልድይ ጥገና የፊታችን ማክሰኞ እንደሚጀመር የዋግኸምራ ብሄረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡