
ባሕር ዳር: ሰኔ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ሕፃናት ቀን “ሰላም፣ ፍቅር፣ እንክብካቤ እና ጥበቃ ለሁሉም ሕፃናት” በሚል መሪ መልዕክት በአፍሪካ ለ33ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ ይከበራል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ቀኑን በተለያዩ ኹነቶች እያከበረ ነው። በከተማው ውስጥ የሚገኙ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ልጆች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን አቅርበው የማበረታቻ ሽልማቶች ተሰጥቷቸዋል።
ለችግር ተጋላጭ የኾኑ ሕፃናትን ከረጅ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ጋር ተገናኝተው ድጋፍ እንዲያገኙም ተደርጓል። የሕፃናትን ተጋላጭነት በመቀነስ ዙሪያም ውይይት ተደርጓል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ የሻረግ ፈንታሁን ሕፃናትን ከጥቃት እና ከተለያዩ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች መጠበቅ የሁሉንም ዜጎች ርብርብ የሚፈልግ ተግባር ነው ብለዋል።
ሕጻናት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ እና ለሱስ እንዳይጋለጡ ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል። ኀላፊዋ ለችግር ተገላጭ የኾኑ ሕጻናትን በቋሚነት በመደገፍ ለሀገር ውለታ የሚከፍል ዜጋ ለማፍራት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። ለዚህም ረጅ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የተለመደው ሕጻናትን የመደገፍ ኀላፊነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፍትሐ ነገስት በዛብህ ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ባለፈችባቸው ዓመታት ሴቶች እና ሕጻናት የበለጠ ተጎጅ ነበሩ ብለዋል። በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጎዳና የወጡ ሕፃናትን ወደ ቤት የመመለስ ሥራ በትኩረት መሠራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
ሕፃናትን ይዘው በድህነት ምክንያት ቤት ንብረት ያጡ ወላጆች መጠለያ እንዲያገኙ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ቀጣይ ርብርብ ማድረግ አለባቸውም ብለዋል። ሕጻናት በትምህርት እና በሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።
በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ የሕጻናት የሥራ ክፍል ኀላፊ ሰለሞን ካሳ በከተማው 11 ሺህ 630 ለችግር የተጋለጡ ሕፃናት ተለይተዋል ብለዋል። እነዚህ ሕፃናት በተለያዩ ምክንያቶች ቤተሰብ የሌላቸው እና ረዳት ያጡ ናቸው። 2 ሺህ 150 የሚኾኑ ኑሮአቸው በጎዳና ላይ የሆኑ ልጆች በከተማው እንዳሉም ጠቅሰዋል። ከዚህ ውስጥ 235 ያህሉ ሴቶች ናቸው።
አቶ ሰለሞን በባሕርዳር ከተማ ውስጥ ኑሮአቸው በጎዳና ላይ የኾኑ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው ብለዋል። የችግሩን አሳሳቢነት በውል በመገንዘብ እና በመደጋገፍ አስከፊውን የጎዳና ኑሮ የሚገፉ ልጆችን ቁጥር መቀነስ ያስፈልጋል ብለዋል። አቶ ሰለሞን መምሪያው በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሕጻናትን ወደ ቤታቸው ለመመለስ በሚችለው ሁሉ እየሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
1 ሺህ 92 ለሚኾኑ ልጆች ቋሚ፣ 9 ሺህ 472 ለሚኾኑት ደግሞ ጊዜያዊ ድጋፍ እየተደረገ ስለመኾኑም አንስተዋል። አቶ ሰለሞን መምሪያው ሕጻናትን ለመንከባከብ የሚያደርገውን ጥረት መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች በመጠኑ እያገዙ ነው ብለዋል። ሕጻናትን በዘላቂነት ከችግር አውጥቶ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ለማድረግ የኅብረተሰቡ ድጋፍ የማይተካ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ዘጋቢ :- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!