የአማራ ክልል ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት በዘርፉ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳሰበ።

46

ባሕር ዳር: ሰኔ 2/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በጣና ዙሪያ በሚገኙ 10 ወረዳዎችና 60 ቀበሌዎች ላይ ተሳትፏዊ የዓሣ ሃብት ልማት አሥተዳደር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱንም ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።

በገጸ-ምድርና በከርሰ- ምድር ውኃ ጸጋ የታደለው የአማራ ክልል በዓሣ ሃብት ልማት በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ሥራዎች የሚከናወኑበት ነው ተብሏል።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለማስቆም ታላሚ ተደርጎ የተዘጋጀ የቀበሌ አሥተዳዳሪዎች፣የጸጥታ አካላት፣የንግድና ገበያ ልማት ተቋም አካላት እና ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የውይይት መነሻ ጹሑፍ ያቀረቡት በአማራ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ጽፈት ቤት የዓሣ ቴክኖሎጅ ባለሙያው አበበ ፈንታሁን እንዳሉት በተያዘው ዓመት ከ27 ሺህ 870 ቶን በላይ ዓሣ ማምረት መቻሉ ገልጸዋል።

ይህም የዕቅዱን 81 በመቶ ማሳካት መቻሉን ነው የተናገሩት። በአማራ ክልል የዓሣ ልማት ሥራውን በአግባቡ መምራት ከተቻለ በዓመት ከ30 ሺህ እስከ 40 ሺህ ቶን ዓሣ ማምረት እንደሚቻል ነው የተገለጸው።

በውይይቱ የዓሣ ልማትን ለማሳደግ የዓሳን ተፈጥሯዊ ኹኔታውን መረዳት እንደሚገባ ነው የተነገረው።

ከግንቦት እስከ ሐምሌ ወር መጀመሪያ በጣና ሐይቅ የዓሳ መራቢያ ወቅት በመኾኑ የዓሳ ማስገር ሥራው ዝግ የሚኾንበት ወቅት ነው ተብሏል።

የዓሳ ቴክኖሎጂ ባለሙያው አበበ ፈንታሁን እንዳሉት በዋናነት የዓሳ ሃብት ልማቱን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳው ያለው ያልተፈቀዱ የዓሣ ማስገሪያ መረቦች እና ሕገ ወጥ የዓሣ አስጋሪዎች መበራከት ዘርፉን እየፈተኑት ነው ብለዋል።

ሞኖፊላሜንት መረብ፣ተጎታች መረብ፣መርዛማ እጽዋቶች፣ዓሣ አስካሪ ኬሚካሎችና መሰል ሕገ ወጥ የዓሣ ማስገሪያ መሳሪያዎችን መጠቀም ለዓሳ ዝርያው መጥፋት መንስኤ ናቸው ነው ያሉት። እነዚህን ተግባራት በሕግ የተከለከሉ መኾናቸውን መረዳት ይገባል ተብሏል፡፡

ለውጤታማ ዓሣ ሃብት ልማት ሥራው ሕገ ወጥነትን ለመከላከል ሙያዊ አሠራርን መከትል እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዘጋቢ :- ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ለማስቀረት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል” የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next article“በቀጣይ 20 ቀናት ውስጥ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ይደርሳል” ግብርና ሚኒስቴር