“ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ለማስቀረት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል” የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

76

ባሕር ዳር: ሰኔ 2/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ለማስቀረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

“በተጠናከረ የማኅበረሰብ ተሳትፎ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ እንከላከል” በሚል ሀገር አቀፍ ውይይት በድሬደዋ እየተካሄደ ነው።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ ታዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት እየተካሄደ የሚገኘው ውይይት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ሕገ-ወጥ ስደት የመከላከል ቅንጅታዊ ሥራን ይበልጥ ለማጠናከር ነው።

በሀገር ውስጥ አማራጭ የሥራ ዕድል ባለበት ሁኔታ ዜጎች ሥራ ፍለጋ ሕገ-ወጥ ጉዞን አማራጭ በማድረግ ለከፋ ማኅበራዊና ሰብዓዊ ችግሮች እየተዳረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

ችግሩን ለመከላከልና ለማስቀረት ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ዜጎች ድርጊቱን እንዲጠየፉና በአማራጭ የሥራ ዕድሎች እንዲጠቀሙ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሳተፉ አካላት እና ቡድኖችን በተቀናጀ መንገድ ትስስራቸውን በመበጣጠስ ለሕግ የማቀረቡ ስራ ከፍትህ ተቋማት ጋር እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተገኝተዋል።

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፅሁፍና በቀጣይ ሀገራዊ ንቅናቄውን ህዝባዊ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድ ላይ ምክክር እንደሚደረግ ተመልክቷል።

በተጨማሪም በሰዎች መነገድና በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል መከላከልን አስመልክቶ በወጡ የሕግ ማዕቀፎች ላይ የተዘጋጁ ፅሁፎች እንደሚቀርቡም ይጠበቃል።

በውይይቱ የፌዴራልና የክልሎች እንዲሁም የከተማ አስተዳድሮች ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተፈራረቁብንን ችግሮች በመቋቋም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በቁጭት እየተዘጋጀን ነው” የአጣዬ ከተማ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች
Next articleየአማራ ክልል ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት በዘርፉ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳሰበ።