
ባሕር ዳር: ሰኔ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአጣዬ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ2015 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ በአካባቢው በተፈጠሩ ተደጋጋሚ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት አስቸጋሪ ጊዜያትን ያሳለፉ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
ተማሪ ማርታ ኀይሉ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪ ናት። ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት በከተማው ከ10 ጊዜ በላይ በፀረ ሰላም ኀይሎች ጥቃት መሰንዘሩን አንስታ በዚህም ምክንያት ለበርካታ ጊዜያት የመማር ማስተማር ተግባሮች ሲቋረጡ መቆየታቸውን አስረድታለች፡፡
የሰላም እጦቱ ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዳይማሩና ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና እንዲደርስባቸው ማድረጉን ነው ያብራራችው፡፡
ሌላው የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ሸጋው ደርብ በርካታ ተማሪዎች በነበሩ ጦርነቶች ቤተሰቦቻቸውን በማጣታቸው ብሎም የቤተሰቦቻቸው ቤት በመቃጠሉ የደረሰባቸው የሥነ ልቦና ጫና ከባድ መሆኑን ገልጿል፡፡
ለቀጣዩ ፈተናም “የተፈራረቁብንን ችግሮች በመቋቋም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በቁጭት እየተዘጋጀን ነው” ብለዋል፡፡
ለዚህም መምህራን በችግሮች ውስጥም ኾነው የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉላቸው ስለመኾኑም ተናግረዋል።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በሪሁን እሸቱ ትምህርት ቤታቸው ከዚህ ቀደም የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ሞዴል እንደነበረ አንስተው በ2014 የትምህርት ዘመን ግን በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ጥሩ ውጤት አለማስመዝገቡን ነው ያብራሩት፡፡
ውጤቱ በመምህራንና በትምህርት ተቋሙ ላይ ከፍተኛ ቁጭትን ፈጥሯል ያሉት ርዕሰ መምህር በሪሁን ውጤቱን በ2015 የትምህርት ዘመን ለመቀየር የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡
በማጠናከሪያና ማካካሻና በቤተ ሙከራ ትምህርት፣ በቅድመ ምዘናና ተከታታይነት ባለው የክትትል ሥራ መምህራን ከመቼውም ጊዜ በተለየ የተጠናከረ ሥራ እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል።
የኤፍራታና ግድም ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ነጋሽ ጋሻውበዛ እንዳሉት በወረዳው የአጣዬ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በአራት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 1 ሺህ 81 ተማሪዎች ቀጣይ የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ይወስዳሉ።
ኀላፊው ተማሪዎቹ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የተለያዩ የአሠራር ስልቶች ተቀይሰው በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም ከመምህራን፣ ርዕሳነ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እንዲሁም ከሌሎች አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በመግባባት ተግባሩ በጥብቅ ድጋፍና ክትትል እየተመራ መኾኑን አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ:- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!