
ባሕር ዳር: ሰኔ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሰብል ልማት ዳይሬክተር አግደው ሞላ እንዳሉት በምሥራቅ አማራ በሚገኙ አራት ዞኖች ዘጠኝ ወረዳዎች የተምች ወረርሽኝ ተከስቷል፡፡
የተምች ወረርሽኝ የተከሰተው በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ፣ አላማጣ፣ ባላ፣ ሃብሩ፣ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደዋ ጨፋ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ደግሞ ቀወት፣ በረኸት እና ሸዋ ሮቢት ወረዳዎች በ3 ሺህ 769 ሄክታር መሬት ላይ ነው፡፡
በበልግ ሰብሎች ላይ እና በግጦሽ ሳር ላይ ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ወረርሽኙን ለመከላከል የፌዴራል መንግሥት ወደ ኮምቦልቻ የእጽዋት ክሊኒክ ኬሚካል እያጓጓዘ ይገኛል፤ የክልል መንግሥትም በክልሉ ተከማችቶ የነበረውን ኬሚካል ወደ አካባቢው አጓጉዟል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን የተወሰኑ አካባቢዎችም የመድኃኒት ርጭት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ሞቃታማ አካባቢዎች ሊከሰት የሚችልን የዛፍ አንበጣ ለመከላከል እየተሠራ መኾኑን ነው የነገሩን፡፡
አኹን ላይ በክልሉ የተከሰተውን የተምች ወረርሽኝ ለመከላከል ሁሉም እንዲረባረብ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!