
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ በነጻነት በቆሙበት ምድር ላይ ፈጽሞ ይጠፉ ዘንድ የዘር ማጽዳት ዘመቻ መንግሥታዊ መዋቅር ተዘርግቶለት ተፈጽሟል፡፡ አካባቢው ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ለአማራ ሕዝብ ምድራዊ ሲኦል ኾኖ ቆይቷል፡፡ ዓለም እስከ ዛሬ ድረስ ገና ያልሰማው ብዙ ግፍ እና መከራ፤ በደል እና ጥቃት በቡድን እና በተናጠል አልፏል፡፡ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለመፈጸም ቀርቶ ለማሰብ የሚከብድ ጥቃት፤ ለመቀበል ቀርቶ ለመስማት የሚዘገንን ጭፍጨፋ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አማራዎች ላይ ተካሂዷል፡፡
“ብሶት የወለደን ነን” ያሉት የአንድ ሰፈር ታጋዮች ገና ጫካ እያሉ በትረ መንግሥቱን ሳይቆጣጠሩ አንድን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ጠላት ብለው ፈረጁት፡፡ 1960ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ባዘጋጁት የጫካ ማኒፌስቶ ከሌሎች ወንድም ሕዝብ ጋር ሀገሩን በተጋድሎ ያቆየው የአማራ ሕዝብ “ጠላት” ተብሎ ተፈረጀ፡፡ ክፉና ደጉን አብሮ ያሳለፈ ሕዝብ ለዘመናት በዘለቀ መርዘኛ ጥላቻ ውስጥ እንዲያልፍ ተገደደ፡፡ ትግሬ እንጂ ትግራይ ተከዜን ተሻግራ አታውቅም ቢባሉም “ታላቋን ትግራይ” ለመመሥረት በሚል የቀን ቅዥት ከሰው ይልቅ ለመሬት ቅድሚያ ሰጥተው በሰብዓዊነት ላይ መረማመድን መረጡ፡፡
ወቅቱ ሀገሪቱን ይመራ የነበረው ወታደራዊ መንግሥት ደርግ በምሥራቅ ኢትዮጵያ የተቃጣበትን የኅልውና ጦርነት ለመመከት ሙሉ ትኩረቱን በዚያው አካባቢ ያደረገበት ነበር፡፡ የመንግሥትን መድከም እና የአካባቢውን ሕዝብ ቅንነት እንደ መግቢያ ቀዳዳ ተጠቅመው ወንዝን በገመድ እየተንጠላጠሉ ትንኮሳ ሲጀምሩ ከጣሊያን የከፋ ጠላት ከአብራካችን ክፋይ ይወጣል ብለው ያላሰቡት የወልቃይት አማራዎች የመጣውን ከመመለስ የዘለለ እርምጃ አይወስዱም ነበር፡፡ ነገር ግን ትንኩሳው ሲደጋገም ተንኳሾቹ ከወዴት መጡ የሚል ጥያቄ ያነሱት የአካባቢው ነዋሪዎች ከተከዜ ወዲያ ማዶ አንድ የመሸገ ኀይል እንዳለ ደረሱበት፡፡
ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ እና በራያ አካባቢ የተፈጸሙት ዘርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ሁሉ መዋቅራዊ ናቸው ያሉን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ ናቸው፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ወረራ እና መዋቅራዊ ዘር ማጥፋት ጥናት ቡድን መሪ ናቸው። በወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት እና ራያ አካባቢ በሚኖሩ አማራዎች ላይ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት የተፈጸመውን ዘር ተኮር ጥቃት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሳይቀር እውቅና ነበራቸው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ፤ የዘር ማጽዳት ዘመቻው መዋቅራዊ ስለነበር በቀላሉ ማስቆም ሳይቻል ቆይቷል ይላሉ፡፡
የጥናት ቡድን መሪው እንደሚሉት ከ1974 ዓ.ም በፊት በነበሩት ትንሽ ዓመታት የነበረውን ፈታኝ ጊዜ የአካባቢው ነዋሪዎች በሚያስገርም ጀግንነት መመከታቸውን አንስተው ለዚህ እንደማሳያ ተደርጎ የሚቀርበው ራሳቸው ተስፋፊዎቹ ሳይቀር ከ50 ሺህ በላይ ወራሪዎቻቸው በአካባቢው ጀግኖች እንደቀሩባቸው ማንሳታቸው ነው፡፡ ነገር ግን “ታላቋን ትግራይ” የመመስረት ዓላማ ይዘው የተነሱት ኅይሎች በሂደት አቅም እየፈጠሩ መምጣታቸውን ተከትሎ ፍልሚያው እጀ ረጂም በኾነ መንግሥት እና በአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል በመኾኑ የኀይል ሚዛኑ የወራሪዎች እየኾነ መጣ ይላሉ፡፡
የደርግ መንግሥት ወድቆ አዲስ ሥርዓት ከተተካ በኋላ በወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ፣ ጠለምት እና ራያ አካባቢዎች “አማራ ነን” ማለት በግልጽ የሚያስጨፈጭፍ ማንነት ኾነ የሚሉት ቡድን መሪው በየአካባቢው የጅምላ መቃብሮችን መመልከት አዲስ ነገር አይደለም ይላሉ፡፡ እልፎች ስለማንነታቸው በጀግንነት በአደባባይ በተገደሉባቸው በእነዚህ አካባቢዎች በርካቶች በግፍ ተሰቃይተዋል፣ ሀገር እንዲለቁ ተገድደዋል፤ አንዳንዶቹም እድሜ ዘመናቸውን በጫካ ውስጥ ለነጻነት እና ለማንነት ዋጋ እየከፈሉ ኖረዋል፡፡ ይኽ ሃቅ በጥናት የተረጋገጠ እና በበቂ መረጃ የተደገፈ ነው ብለውናል፡፡
ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ብቻቸውን “አማራ ነን እንጂ፤ አማራ እንሁን አላልንም” እያሉ ዘመናቸውን ሁሉ በትግል ያሳለፉት የወልቃይት አማራዎች የግፍ ጽዋው ሞልቶ ሲፈስስ ነጻነታቸውን አወጁ ነው ያሉት፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ ባለፉት ሦስት ዓመታት የወልቃይት ሕዝብ መብራት አጥቶ በጨለማ ውስጥ እያለፈ እንኳን በብርታት የሚሠራው ነጻነቱን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማረጋገጥ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ዘመን በጀት አልባ የመንግሥት ሥርዓትን ለዓመታት ያጸና ሕዝብ ከወልቃይት እና ራያ በቀር አልታየም፤ ይህ ደግሞ ነጻነታቸውን ከማንም እና ከምንም በላይ ማስቀደማቸውን የሚያመላክት ነው ይላሉ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ ከሰሞኑ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የሰብዓዊ መብት ድርጅት አካባቢውን በሚመለከት ያወጣው መረጃ “ከሳሽ ሲሽኮረመም ተከሳሽ ይኾናል” አይነት ነው ይላሉ፡፡ ካሳ የሚያስፈልገው ሕዝብ እና አካባቢ መካሱ ቀርቶ በሕግ ማግኘት የሚገባውን በጀት አላገኘም፡፡ ገዳዮቹ ለሕግ መቅረብ ሲገባቸው ለሀገራዊ ሠላም ሲባል ዝም ከተባለ፣ በስደት እና በግፍ የኖረ ሕዝብ መብራት፣ ትምህርት ቤት፣ የንጹህ ውኃ አቅርቦት፣ የጤና ተቋማት እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ሳይሟሉለት ነጻነቱን ብቻ እያጣጣመ ከተቀመጠ ሃቅ ተገልብጦ መቅረቡ አይቀሬ ነው ይላሉ፡፡
መንግሥት ለአምነስቲ ምላሽ ከመስጠት ባሻገር ከአምነስቲ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ መሥራት ይኖርበታል ያሉት ቡድን መሪው፤ የአምነስቲ የመረጃ ምንጭ እና ዘዋሪዎች እነማን እንደኾኑ ግልጽ ነው ብለዋል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሊፈጠሩ የሚችሉ ሀገራዊ ለውጦችን በማሰብ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እና የእርዳታ ድርጅቶችን አስገብተው ሰግስገዋል፤ ይህንን በዘላቂነት ለመፍታት ተቀራርቦ መሥራት እና የአካባቢውን ሕዝብ ጥያቄ በሚገባ መመለስ ነው፡፡ አምነስቲም ኾነ ለሌሎቹ ከሰብዓዊነት ይልቅ ፖለቲካን ለሚያስቀድሙ ድርጅቶች በቂ ምላሽ የሚኾነው መንግሥት ከታሪክ፣ ከእውነት እና ከማንነት አንጻር አይቶ ፈጣን ውሳኔ ሲያሳልፍ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!