“አካባቢያችንን ከፕላስቲክ ቆሻሻ በመጠበቅ ለመጭው ትውልድ ንጹህ ምድር ማውረስ አለብን” አቶ ተስፋሁን አለምነህ

56
ባሕር ዳር : ሰኔ 1/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ50ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ለ30ኛ ጊዜ፤ በአማራ ክልል ደግሞ ለ26ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም አካባቢ ቀን በባሕርዳር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ የሥራ ኀላፊዎች በባሕርዳር ከተማ ተገኝተው የወዳደቁ የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን አጽድተዋል። ከሰዓት በኋላም በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል። የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊ ተስፋሁን አለምነህ “አካባቢያችንን ከፕላስቲክ ቆሻሻ በመጠበቅ ለመጭው ትውልድ ንጹህ ምድር ማውረስ አለብን” ብለዋል።
ኀላፊው አሁን ላይ አካባቢያችን ከፍተኛ ቁጥር ባለው የፕላስቲክ ቆሻሻ እየተሞላ መኾኑ ስጋት ፈጥሯል ነው ያሉት። ችግሩ በዚህ ከቀጠለ የውኃ አካላት ጭምር በፕላስቲክ ቆሻሻ ክምችት ተበክለው የብዝሐ ሕይወት መቃወስ እንደሚገጥም ተናግረዋል። በመኾኑም የምንጠቀማቸውን የፕላስቲክ ከረጢቶች ሙሉ በሙሉ በጨርቅ መቀየር እንደሚያስፈልግ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የየክልሉ አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን በተሰጠው አካባቢን የመጠበቅ ኀላፊነት መሰረት ዛሬን ሳይኾን ነገን ጭምር ታሳቢ በማድረግ ተፈጥሮን ምቹ የማድረግ ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል። ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን በየአካባቢው ከመጣል ይልቅ መልሶ የመጠቀም ልምድ እንዲፈጠር እያደረግን ነው ብለዋል። በዚህም ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን የኅብረተሰብ ግንዛቤ እና መረጃ ተደራሽነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ በፍታ ጤናው በበኩላቸው በአማራ ክልል ደረጃ የተከበረው የዓለም አካባቢ ቀን ሕዝቡ ከብክለት የጸዳ እና ምቹ አካባቢ የመፍጠር ልምዱን የበለጠ እንዲያሰፋ የሚያስችል ነው ብለዋል። አሁን ላይ ለአካባቢ መጨነቅ እየተለመደ መጥቷል ያሉት ዳይሬክተሯ በተለይም ፋብሪካዎች በሚገነቡበት ወቅት ለከባቢ አየር ብክለት ያላቸውን ተጽዕኖ ቀድሞ ማጥናት እየተለመደ መጥቷል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ምድርን ከብክለት በንቃት የሚጠብቅ ትውልድ እንዲፈጠር እየጣረ ነው ብለዋል። በትምህርት ቤቶች ውስጥ የአካባቢ እንክብካቤ ክበባት ተቋቁመው እየተሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ወይዘሮ በፍታ አካባቢ ሲበከል ተጽእኖው የሚታየው ቀስ በቀስ በመኾኑ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል። ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ ምድር ማስተላለፍ ከዚህ ትውልድ የሚጠበቅ ሃላፊነት በመኾኑ አካባቢያችንን ከፕላስቲክ ቆሻሻ መጠበቅ ያስፈልጋል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየፍሪላንሰር ቅጥር ማስታወቂያ
Next article“ከሳሽ ሲሽኮረመም ተከሳሽ ይኾናል” ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ