ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ 3ኛና 4ኛ ዙር የተረክ በጉርሻ ባለዕድሎችን ሸለመ።

120

ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የተረክ በጉርሻ ሁለተኛ መኪና አሸናፊን፣ ሁለት ባጃጅ፣ ሁለት ሞተር ብስክሌት እና በርካታ ስልኮችን ያሸነፉ የ3ኛ እና 4ኛ ዙር እድለኞችን ሸልሟል፡፡

የመኪና አሸናፊው ከአዳማ፣ ሁለቱ ባጃጅ አሸናፊዎች ደግሞ ከኤረር እና ከዳንግላ፣ ሁለቱ ሞተር ብስክሌት አሸናፊዎች ደግሞ ከዳንግላ እና ከአምቦ የተገኙ ናቸው። ስማርት ስልክ እና ታብሌት አሸናፊዎች ደግሞ በሁሉም ክልል ከተሞች የሚገኙ ሊባል በሚችል ደረጃ የሚኖሩ ናቸው።

መርሐግብሩ መጋቢት 27/ 2015 ዓ.ም ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ከ710 ሺህ በላይ ደንበኞች በየዕለቱ የሚወጡ የአየር ሰዓት ሽልማቶችን እንዳገኙ የሳፋሪኮም የሽያጭ አገልግሎት ማዕከላት ኀላፊ ተናግረዋል ፡፡

የአዳማው ቶላ ጅማ 4ኛው ዙር የሁለተኛው የመኪና ሽልማት አሸናፊ ኾኖ ሚቱሱቡሺ መኪና ተሸልሟል። “ስልክ ደውለው መኪና ማሸነፌን ሲነግሩኝ ማመን አልቻልኩም ነበር፤ እየሆነ ያለውን ነገር ለመቀበል የተወሰነ ጊዜ ወስዶብኝ ነበር። የሳፋሪኮም መስመሬን መጠቀም ከጀመርኩ ወራት የሆነኝ ቢሆንም መኪና ያመጣልኛል ብዬ ገምቼ አላውቅም ነበር ብሏል። ዕድለኛ ሆኜ መኪና በማሸነፌ ደስተኛ ነኝ፤ ሌሎችም ዕድላቸውን እንዲሞክሩ እመክራለሁ።” በማለት ቶላ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የሞተር ሳይክል ሽልማት አሸናፊው ከዳንግላ የመጣው አዲሱ እሸቴ ሲሆን የባጃጅ አሸናፊው ደግሞ ግሩም አስማረ ሆኗል። ሽልማቱን የሳፋሪኮም የማዕከላዊ ሽያጭ ኀላፊ ዳዊት መኮንን ያስረከቡ ሲሆን ተረክ በጉርሻ የተሰኘው የሽልማት መርሐ ግብር ደንበኞች የሳፋሪኮም ሲምካርዳቸውን ሲያወጡ፣ የአየር ሰዓት ሲገዙ እና ጥቅሎችን ሲሞሉ እንዲሁም የዋትሳፕ ጥቅሎችን ሲጠቀሙ፤ ለባለዕድለኛነት ብቁ የሚያደርጋቸው የዕጣ መርሐ ግብር ነው ብለዋል ።

ከሁለት ወራት በፊት በጀመረው የሽልማት መርሐ ግብር በየሁለት ሳምንቱ ደንበኞችን 200 ቅመም ስልኮች፣ 3 ሳምሰንግ ኤስ 21 ስልኮች እና 3 ሳምሰንግ ታብሌቶችን ይሸለማሉ። ይህም በየሁለት ሳምንቱ ለሽልማት ከሚቀርቡት ባጃጆች እና ሞተር ብስክሌቶች፣ በወር አንዴ ለሽልማት ከሚቀርበው መኪና እንዲሁም ዕለታዊ የአየር ሰዓት ሽልማት በተጨማሪ ለደንበኞች የሚሽለም ነው፡፡

የተረክ በጉርሻ የሽልማት መርሐ ግብር የሳፋሪኮም ኔትወርክ አልግሎት ላይ በዋለባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች እስከ ሰኔ 27/ 2015 ዓ.ም ድረስ ይዘልቃል ተብሏል፡፡

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዓላማ መር የቴክኖሎጂ እና የኮሙኒኬሽን ኩባንያ፤ የኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግር እና አካታች አጀንዳ ላይ አስተዋፅኦ ለማበርከት በቁርጠኝነት የሚሠራ ኩባንያ መኾኑም ተገልጿል።

ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን በከፍተኛ ውጤት ለማለፍ ተዘጋጅተናል” ተማሪዎች
Next articleአሜሪካ ለኢትዮጵያ የ112 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ይፋ አደረገች።