“የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን በከፍተኛ ውጤት ለማለፍ ተዘጋጅተናል” ተማሪዎች

78

ባሕር ዳር: ሰኔ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን በጥሩ ውጤት ለማጠናቀቅ መዘጋጀታቸውን አሚኮ ያነጋገራቸው በደቡብ ጎንደር ዞን ጉና በጌምድር ወረዳ የክምር ድንጋይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎቹ እንደነገሩን ለሀገር አቀፍ ፈተናው በግልም ይሁን በጋራ እየተረዳዱ እየተዘጋጁ ነው፡፡

ተማሪ ያለምወርቅ ይርጋ ”በተቃራኒ ፈረቃ፣ ቅዳሜና እሑድን ጨምሮ መምህራን ጥያቄዎችን በመሥራት እያገዙን ነው” ብላለች፡፡

መምህራን ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ በምክር በማበረታታት ተማሪዎችን ለማብቃት እየጣሩ መኾኑን የጠቀሰው ደግሞ ተማሪ ሳለአምላክ ክንዱ ነው፡፡ ”የምንወዳደረው ከኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጋር በመኾኑ ጠንክረን እያጠናን ነው፤ የጎበዝ ተማሪዎች ውጤት እንዳይበላሽ ለማድረግም አዲሱ የአፈታተን ሥርዓት ጥሩ ነው” ብሏል፡፡ ተማሪ ሳለአምላክ ባለፈው ዓመት በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የመፈተኛ ጣቢያ የታየው የተፈታኞች ብልሹ ምግባር መደገም እንደሌለበትም አሳስቧል፡፡

የተጀመረው የአፈታተን ሥርዓት ትምህርታቸውን ጠንክረው ለሚማሩ ተማሪዎች ጥሩ ከመኾኑም በላይ ለትምህርት ጥራት አጋዥ ስለኾነ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ተማሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡

በጉና በጌምድር ወረዳ ሁለት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 1 ሺ106 ተማሪዎችን እንደሚያስፈትኑ የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበራ ኢሳያስ ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎች ፈተናውን በብቃት አልፈው ወደ ዩኒቨርሲቲዎች መግባት እንዲችሉ የቀለም ዕውቀትና የሥነ ምግባር ዝግጅት እየተደረገ መኾኑንም ነው የተናገሩት፡፡

”ያለፈው ዓመት የተማሪ እገዛችን ምን ይመስል ነበር በሚል ከተማሪ ወላጅና መምህራን ጋር ገምግመናል፤ ተፈታኝ ተማሪዎች ከባለፈው ዓመት ችግር ትምህርት በመውሰድ እንዲዘጋጁ አቅደን ወደ ሥራ ገብተናል” ብለዋል።

የጽሕፈት ቤት ኀላፊው ተማሪዎችና መምህራን ዕውቀት ነክ ዝግጅት እንዲያደርጉ እስከ አንድ ሺህ ጥያቄዎች ተዘጋጅተው ቤተ መጽሐፍት ላይ እንዲቀመጡ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
አቶ አበራ የቴሌግራም መገናኛ በመፍጠርና ጥያቄዎችን በቴሌግራም በመጫን፣ ቤተ መጽሐፍት ቅዳሜና እሑድን ጨምሮ ለጥናት ምቹ በማድረግ፣ በጎ ፈቃደኞችና መምህራን ቅዳሜና እሑድ እንዲያስተምሩ መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

ተማሪዎች የሥነ ምግባር ችግር እንዳይኖርባቸውም ከራሳቸው ከተማሪዎች፣ ከወላጆች፣ ከመምህራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ኮሚቴ በማቋቋም በየ3 ወሩ ምክክር መደረጉንም አቶ አበራ ተናረዋል፡፡
የጉና በጌምድር ወረዳ አሥተዳዳሪ ጌትነት አስናቀ በወረዳው ለትምህርት ጥራት ትኩረት በመሥጠት ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በትምህርት ላይ የሚሠሩ የሥራ ኀላፊዎችን ከሌሎች የወረዳው ሥራዎች ነጻ በማድረግ የትምህርትን ተግባር ብቻ እንዲመሩ ተደርጓል ነው ያሉት። የሰው ኀይል በማሟላት፣ በየ3 ወሩ የትምህርትን ሥራ በመገምገም ወረዳው ለትምህርት ጥራት ትኩረት መስጠቱንም ነው ያስረዱት፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ታደለ ሙጬ በዞኑ በ14 ወረዳዎች 55 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 19 ሺህ 73 ተማሪዎችን እንደሚያስፈትኑ ገልጸዋል፡፡ ተፈታኞች በቂ ዕውቀት እንዲይዙና ባለፈው ዓመት የፈተና ወቅት ያጋጠመው ችግር እንዳይደገም ዝግጅት መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡

አቶ ታደለ በ53 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለቤተ መጽሐፍት አስነባቢዎች የትርፍ ጊዜ ክፍያ በመክፈል ቤተ መጽሐፍት ቅዳሜና እሑድ ክፍት እንዲኾኑ መደረጉን ተናግረዋል። ተማሪዎች መጽሐፍትን ከቤተ መጽሐፍት አውጥተው ቤታቸው ወስደው ማንበብ እንዲችሉ፣ ከፍተኛ ውጤት ሊያስመዘግቡ ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁ ተማሪዎችን ለአቅማቸው የሚመጥን ጥያቄ እየቀረበላቸው በጋራ እንዲያጠኑ ልዩ ድጋፍ መደረጉንም በአብነት አንስተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በፈተና ወቅት ያጋጠመው የተማሪዎች የሥነ ምግባር መጓደል እንዳይደገም በወላጆች፣ ተማሪዎችና መምህራን ኅብረት በኩል ሰፊ ምክክርና ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል፡፡
በዞኑ ዘንድሮ 19 ሺህ 73 መደበኛ ተማሪዎች፣ 6 ሺህ 615 የማታና የግል ተፈታኞች በድምሩ 25 ሺህ 688 ተፈታኞች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለመውሰድ ፎርም መሙላታቸው ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ ደመቀ መኮንን አይ ኤስ አይ ኤስን ለመዋጋት በተቋቋመው ዓለም አቀፍ ጥምረት የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ነው።
Next articleሳፋሪኮም ኢትዮጵያ 3ኛና 4ኛ ዙር የተረክ በጉርሻ ባለዕድሎችን ሸለመ።