
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 19/2012ዓ.ም (አብመድ) የ9ኛ ክፍል ተማሪው ያለሰው ረዳት እንጀራ መጋገር የሚችል ሮቦት ሰርቶ ለእይታ አቅርቧል፡፡
ተማሪው የሰራው ሮቦት በቤት ዉስጥ እንጀራ ለመጋገር ያለውን እንግልትና ድካም የሚያቃልል ነው፡፡ ሮቦቱ ሁሉንም እንጀራ ለመጋገር የሚያስፈልጉ ሂደቶች ያለማንም ርዳታ ይከውናል፡፡
ከደብረ ብርሃን ከተማ በ65 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሞረትና ጅሩ ወረዳ እነዋሪ ከተማ ላይ ተገኝተናል። ከዚህ ቦታ ላይ መገኘታችን ምክንያቱ የተማሩትን የቀለም ትምህርት ወደ ተግባር የለወጡ የተግባር ተማሪዎች መኖራቸውን ሰምተን ነው፡፡ እነዋሪ ሚሊኒዬም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቀለምን ከማስቆጠር በዘለለ ተማሪዎችን የተግባር ሰው እንዲሆኑ የሚጥሩ ምስጉን መምህራን ይገኙበታል፡፡
ተማሪዎቹም የመምህራኖቻቸውን ጥረት ወደተግባር በመቀየር ራሳቸውንም ይሁን መምህራኖቻቸውን አንቱ ማሰኘት ጀምረዋል፤ ‹‹አሳዳጊህን ይባርከው›› አይደል የሚባለው፤ አስተማሪም ወላጅም አሳዳጊ ናቸውና አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
በትምህርት ቤቱ ውስጥ ብዙ የፈጠራ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም ቀልባችን የሳበውንና የብዙ ኢትዮጵያውያን እናቶችን የቤት ውስጥ ልፋት የሚያስቀረውን የእንጀራ መጋገሪያ ሮቦት ፈጠራ ልንነግራችሁ ነው፡፡ የዚህ ፈጠራ ባለቤት ደግሞ የ9ኛ ክፍል ተማሪው ዳዊት አድማሱ ነው። ዳዊት ሁሉን አቀፍ ያለማንም ረዳት የሚሠራ የእንጀራ መጋገሪያ መሳሪያ (ማሽን) መሥራቱን አጫውቶናል፤ አሳይቶናል።
በተግባር ሰርቶ እንዲያሳየን ጠይቀነውም መሳሪያዉ ያለሰዉ እገዛ የሚሠራ እንደሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ለኩሶ አሳየን። ‹‹እንጀራ ለመጋገር ከምንከተላቸዉ ሂደቶች የጤፍ ዱቄትን ከማቡካት ጀምሮ አብሲት መጣልና ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ጨምሮ በተገጠመለት ምጣድ ለክቶ መጋገርንና በመጨረሻም የበሰለውን እንጀራ ማዉጣትን ድጋፍ ሳያስፈልገዉ ልክ እንደ ሰው ማከናወን እንዲችል ተደርጎ የተሠራ ነዉ›› ብሎናል የፈጠራው ባለቤት።
ማሽኑ በ”ሴንሰር” ቴክኖሎጂ በራሱ ጊዜ ምላሽ እንዲሰጥ ሆኖ የተሠራ ነው። መሳሪያዉ ‹ሁሉን አቀፍ› ተብሎ የተሰየመ የመንስ ቤት ሥራዎችን ሁሉ የሚከውን ነው፤ እንጀራ ከመጋገር በተጨማሪ የዳቦ መጋገሪያና ሻይ ማፍያም የተገጠመለት ነዉ። ተማሪ ዳዊት መሳሪያዉን የመጨረሻዉ ዉጤት ላይ ደርሶ እንዲታይ ለማስቻል በዋናነት ምጣድ፣ ላሜራ፣ ”ዜድ” ብረት፣ የኤሌክትሪክ አስተላላፊ (ኮንዳክተር)፣ ፓንፕ፣ ዲናሞ፣ ሽቦ፣ ተጠቅሟል። ቁሳቁሶቹን በቀላሉ ለማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንበትም በአካባቢዉ የሚያገኛቸውን በመጠገንና ገዝቶ አገልግሎት ላይ እንዳዋለም ነግሮናል።
የሴቶችን የቤት ዉስጥ እንግልትና ድካም ለማቃለል በማሰብ ይህን መሳሪያ ሊሰራ እንደቻለ ተማሪ ዳዊት ተናግሯል። መሳሪያዉ አሁን ባለበት ደረጃ የሰዎችን አድናቆት እና አበጀህ የሚሉ ምላሾችን አግኝቷል፤ ‹‹አሻሽዬ ሁሉን አቀፍ ያለማንም እርዳታ የሚሠራዉን የእንጀራ መጋገሪያ መሳሪያ ንድፍ (ዲዛይን) አዘጋጅቻለሁ፤ በገንዘብ እጥረት እንጂ ወደፊት በብዙ አሻሽሎ ለገበያ ለማቅረብ ሐሳቡ አለኝ›› ብሏል ተማሪው።
በቀጣይ የጫማ አስዋቢዎችን (የሊስትሮ ሠራተኞችን) ድካም የሚያስቀር የፈጠራ ሥራ ይዞ ብቅ እንደሚልም ነግሮናል። የዳዊት መምህር ኃይሉ ወልደጻዲቅ ‹‹እኛ የተለየ ነገር ባናደርግለትም፣ በአይዞህ ብቻ ብንደግፈዉም ዳዊት በራሱ ተነሳሽነት የሚሰራ ወጣት ነዉ፤ ተሰጥኦ አለዉ፤ ወደፊት ”ኤሌክትሮኒክስ” ቢማር የበለጠ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ›› ብለዋል። ተማሪ ዳዊት አድማሱ የማኅበረሰቡን ችግሮች የሚያቃልሉ በርካታ በእቅድ የተያዙ ፈጠራዎች እንዳሉትም ነግሮናል።
የተማሪ ዳዊት ወላጆችም ልጃቸው አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት ሲያደርግ ከጎኑ በመሆን ማበረታቻ እንደሚያደርጉለት እና የሚፈልገውን ድጋፍ እንደሚሰጡት ነው የነገሩን፡፡
እኛም ተማሪ ዳዊት የሠራው የፈጠራ ሥራ በሌሎች ተደግፎ ቢሠራ የተሻለ ውጤት እንደሚያመጣ ታዝበናል፡፡
ዘጋቢ፡-ኪሩቤል ተሾመ