
ባሕር ዳር : ሰኔ 1/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም አካባቢ ቀን በየዓመቱ ግንቦት 28 ቀን በሁሉም የዓለም አካባቢዎች ይከበራል። በዚህ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ50ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ እና በአማራ ክልል ደግሞ ለ26ኛ ጊዜ ይከበራል።
በአማራ ክልል ደረጃ በባሕርዳር ዙሪያ ሮቢት ቀበሌ “የጨርቅ ከረጢቶችን በመጠቀም የፕላስቲክ ብክለትን እንከላከል” በሚል መሪ መልዕክት እየተከበረ ነው። ቀኑ ሲከበር ከሁሉም አካባቢዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች እና የሥራ ኀላፊዎች የወዳደቁ ፕላስቲኮችን አጽድተዋል። በመቀጠልም በባሕርዳር ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ የወዳደቁ የፕላስቲክ ውጤቶችን በማንሳት ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ያከናውናሉ። በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ያተኮረ የፓናል ውይይትም ይካሄዳል።
የሮቢት እና ጎንባት ቀበሌዎች ለችግኝ ማፍያነት እና ለሌሎች ጉዳዮችም ፕላስቲክ በስፋት ጥቅም ላይ ስለሚውል ብክለቱም የዚያኑ ያህል ነው። በአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አቶ አወቀ ይታይ የፕላስቲክ ውጤቶች በቀላሉ ወደ ብስባሽነት ስለማይቀየሩ አካባቢን በከፍተኛ ኹኔታ እየበከሉ ነው ብለዋል። በመኾኑ በፕላስቲክ አጠቃቀም እና አወጋገድ ላይ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ብለዋል።
ዳይሬክተሩ በቆሻሻ መልክ በየቦታው እየተጣሉ አካባቢን የሚበክሉ የፕላስቲክ ውጤቶችን በማሰባሰብ እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!