ያገለገሉ ፕላስቲኮችን በየቦታው ባለመጣል የአካባቢን ብክለት መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

66

ባሕር ዳር : ግንቦት 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብዝሐ ሕይዎት መመናመንን ተከትሎ የተፈጠረው የአየር ንብረት ለውጥ በምዕተ ዓመቱ የሰው ልጅ እያጋጠሙት ካሉ ፈታኝ ችግሮች መካከል ቀዳሚው ጉዳይ እንደኾነ ይነሳል፡፡ ጠንካራ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እና የተቀናጀ ዘርፈ ብዙ ትብብር ከሚጠይቁ የዓለማችን ቀዳሚ አጀንዳዎች መካከል የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም ተጠቃሽ ፈተናዎች ናቸው ይባላል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ የዓለም ፖለቲካ ሚዛንን ቀልብ እየሳበ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥን እና የአካባቢ ብክለትን “በፕላኔታችን ላይ የተቃጣ ጦርነት ነው” የሚሉትም አልታጡም፡፡ የጉዳቱ ገፈት ቀማሾች ደግሞ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት መኾናቸው ጉዳዩን ከፍትሐዊነት አንጻር ለማየት አስገዳጅ አድርጎታል፡፡

ሀገራት የአካባቢ ብክለት እና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ከሚያደርጉት ፖለቲካዊ ርብርብ በዘለለ ዜጎች አካባቢያቸውን ከሚበክሉ ልማዶች መጠበቅ አለባቸው ተብሎም በምክረ ሃሳብ ደረጃ ይቀርባል፡፡ የሰው ልጅ ዙሪያ መለስ እንቅስቃሴ እና የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት በተፈጥሮ ሥነ-ምህዳር ላይ የተለያዩ ተጸዕኖዎችን እንደሚያሳድር የዘርፉ ምሁራን ያነሳሉ፡፡

ያገለገሉ ፕላስቲኮችን በየቦታው መጣልም ሌላው የአካባቢ ስጋት ከኾነ ውሎ አድሯል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እነዚህ ፕላስቲኮች አገልግሎት ከሰጡ በኃላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ይበሰብሳሉ ወይም ወደ አፈርነት ይቀየራሉ? የሚለው ጥያቄ ግን እስካሁን ቁርጥ ያለ ምላሽ አላገኘም፡፡

ታዲያ ለአካባቢ ብክለት ከፍተኛ ስጋት የኾነውን ያገለገሉ ፕላስቲኮች ችግር እልባት ለመስጠት ዓለም ፣ ዓለም አቀፉን የአካባቢ ቀን በየዓመቱ ግንቦት 28 ያከብራል፡፡ የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ቀን አከባበር እንደ ምዕራባዊያኑ የዘመን ቀመር 1972 ከተካሄደው የስቶክሆልም ጉባዔ ጋር ይገጣጠማል፡፡ ዘንድሮ ለ50ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው የዓለም የአካባቢ ቀን እንደ አህጉር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካዊቷ ሀገር ኮትዲቯር “መፍትሄ ለፕላስቲክ ብክለት” በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሮ ነበር፡፡ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ለ30ኛ ጊዜ የአካባቢ ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች ከሰሞኑ አክብራለች፡፡

በአማራ ክልል ደግሞ የዓለም የአካባቢ ቀን ለ26ኛ ጊዜ “የጨርቅ ከረጢቶችን በመጠቀም የፕላስቲክ ብክለትን እንከላከል” በሚል መሪ ሃሳብ በጣና ሐይቅ እና በዓባይ ወንዝ ዙሪያ እንደሚከበር የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ሲከበር የቆየው የዘንድሮው የዓለም አካባቢ ጥበቃ ቀን ነገ ሰኔ 1/2015 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ይከናወናል፡፡

በአማራ ክልል የሚከበረው የዘንድሮው የዓለም አካባቢ ቀን በጣና ሐይቅ እና በዓባይ ወንዝ አካባቢ መከበሩ ከመሪ ሃሳቡ ጋር ሲታይ የተለየ መልዕክት አለው ያሉት የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊ አቶ ጋሻው እሸቱ የፕላስቲክ ብክለት የሐይቆቻችን እና ወንዞቻችን ህልውና ስጋት እየኾነ መጥቷል ብለዋል፡፡ አቶ ጋሻው የፕላስቲክ ስጋት የምድራችን ሥነ-ምህዳር ፈተና ኾኗል ብለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ400 ሚሊዮን ቶን በላይ ፕላስቲክ እንደሚመረት መረጃዎች ያመላክታሉ ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊው ከዚህ ውስጥ 50 በመቶ የሚኾነው አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ ውሎ እንደሚጣል ይገመታል ብለዋል፡፡ ፕላስቲኮች ዋጋቸው ቀላል፣ ለአያያዝ ምቹ፣ ቦታ የማይዙ እና በቀላሉ ገበያ ላይ የሚገኙ መኾናቸው በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውሉ አስገዳጅ ኾኗል፡፡ እስካሁን ባለ መረጃ ከ19 እስከ 23 በመቶ የሚኾነው የፕላስቲክ ቆሻሻ በውኃማ አካላት ዙሪያ እንደሚጣሉ ይገመታል፡፡ ችግሩን በጊዜ መቆጣጠር ካልተቻለ ለውኃማ አካላት ትልቅ ስጋት ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የዓለም አካባቢ ቀን በዚህ መልኩ መከበሩ የችግሩን አሳሳቢነት ለማሳየት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ያሉት አቶ ጋሻው ከበዓሉ መከበር በኋላ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሁሉንም አጋር አካላት ድጋፍ ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ያገለገሉ ፕላስቲኮች ችግር ከመፍጠራቸው በፊት ሁሉንም አጋጣሚዎች በመጠቀም ባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኮንስትራክሽን ሥራ ለመሠማራት የሚያበቃቸውን ሥልጠና ያጠናቀቁ ባለሙያዎች ወደ ጀርመን ሀገር ሊሠማሩ ነው።
Next articleየዓለም አካባቢ ቀን በባሕር ዳር ዙሪያ ሮቢት ቀበሌ እየተከበረ ነው።