
ዛሬ በኢትዮጵያ የሀንጋሪ አምባሳደር አቲላ ኮፓኒ ከኢፌዲሪ ባሕልና ቱሪዝም ሚንስትር ሂሩት ካሳው (ዶክተር) ጋር በነበራቸው ቆይታ እነዚህን ታሪካዊ ተንቀሳቃሽ ምስሎቹን አስረክበዋል፡፡
ተንቀሳቃሽ ምስሎቹ የተቀዱት ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለሥላሴ በ1965 (እ.ኤ.አ) ሀንጋሪን በጎበኙበት ጊዜ ሙዚቃን በዘመናዊ መሳሪያ የሚቀርፁ ሙያተኞች መኖራቸውን ተመልክተው በኢትዮጵያ ያለውን ባሕላዊ ሙዚቃ የሚቀርፁ ባለሙያዎች እንዲልኩላቸው በጠየቁት መሠረት በዚያው ዓመት የሀንጋሪ የምስልና እና የድምፅ ቀረፃ ሙያተኞች ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት ነበር፡፡
ሙያተኞቹ ጆርጅ ማርቲን እና ባልቲን ሳሮሲ በወቅቱ በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች ማለትም በወሎ፣ ትግራይ፣ ከፋና ወለጋ አካባቢዎች ባሉ በርካታ ከተሞች በመዘዋወር ነበር ሲቀርፁ የቆዩት፡፡ በወቅቱ ከ3 ሺህ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው የፊልም ክሮች፤ ከ40 ሰዓታት በላይ ድምፅ፤ ከ100 በላይ ምስሎችንና ከ200 ገፅ በላይ ጽሑፎችን ቀርፀው ነበር፡፡ በሀንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት በሚገኘው የሀንጋሪ ሳይንስ አካዳሚ የሙዚቃ ጥናት ተቋም ውስጥ የባሕላዊ ሙዚቃና ውዝዋዜዎች ቤተ መዛግብት ተቀምጦ ነበር፡፡
ባሕላዊ ውዝዋዜና ባሕላዊ ሙዚቃዎችን የያዘው ተንቀሳቃሽ ምስል በዘመናዊ መንገድ ዲጂታላይዝ ተደርጎ ለኢትዮጵያ በስጦታ መልክ ተበርክቷል፡፡
በውይይታቸውም ሀንጋሪ እና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት በተለይ በባሕላዊ እሴቶችና በስፖርት ዘርፍ በጋራ መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ በቀጣይም የተወያዩባቸውንና ሌሎች ትብብሮችን ለመፈፀም የሚያስችሉ የመግባቢያ ሰነዶች እንዲዘጋጁ ተስማምተዋል፡፡
አምባሳደሩ በባሕላዊ ቅርሶች አጠባበቅ ዙሪያ በሀንጋሪ አሰልጣኞችየኢትዮጵያ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ፍላጎት እንዳላቸውና እድሉን እንደሚያመቻቹም ለሚኒስትሯ ቃል ገብተዋል፡፡
ምንጭ፡- የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር