
ባሕር ዳር : ግንቦት 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኮንስትራክሽን ሥራ ለመሠማራት የሚያበቃቸውን ሥልጠና ያጠናቀቁ የመጀመሪያው ዙር ባለሙያዎች ወደ ጀርመን ሀገር ሊሠማሩ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አሰታወቀ።
ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በሲቭል ኢንጂነሪንግ፣ በኮንስትራክሽን ማናጅሜንት ቴክኖሎጂ፣ በአርክቴክቸርና መሰል ሙያዎች የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ምሩቃን ወጣቶች ጎኤቴ በመባል በሚታወቀው የጀርመን ባህልና ቋንቋ ኢንስቲትዩት ሥልጠናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።
ሥልጠናው ከዛሬ ሦሥት ዓመት በፊት በቀድሞው ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እና የጀርመን ኮንስትራክሽን ማኅበራት ፌደሬሽን በጋራ እንደተጀመረ ያብራሩት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው።
አቶ ንጉሡ ጥላሁን በጎኤቴ/ጀርመን ባህልና ቋንቋ ኢንስቲትዩት ሥልጠናቸውን አጠናቀው፣ የመጨረሻው ምዘና አልፈውና አስፈላጊውን የሥራ ትዕዛዝ ተቀብለው ወደ ጀርመን ሀገር ለመጓዝ ዝግጀታቸውን ያጠናቀቁትን እንዲሁም በመሠልጠን ላይ የሚገኙትን ምሩቃን በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ግቢ አወያይተዋቸዋል።
አቶ ኤልያስ አብዶ በኢትዮጵያውያ የጀርመን ኮንስትራክሽ ማኅበራት ፌደሬሽን ወኪል በውይይቱ ላይ ፌደሬሽኑን ወክለው፣ ሥልጠናውን የሚከታተሉት ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ከ50 በላይ የሚሆኑ ሠልጣኞች ሲሆኑ ሥልጠናውን ከጀመሩት መካከል 11ዱ ሥልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ የጀርመን ኮንስትራክሽን ፌደሬሽን የሚፈልገውን መስፈርት አሟልተው የመጨረሻውን ፈተና በማለፍ ለጉዞ ዝግጁ የሆኑ ናቸው፡፡
ሁሉንም ሂደቶች ካጠናቀቁት ውስጥ 6ቱ ጀርመን ከሚገኙ አሠሪዎቻቸው ጋር የሥራ ውል ተፈራርመዋል፡፡ የተቀሩትም የሥራ ውል በመጠባበቅና ሥልጠናቸውን አጠናቀው የመጨረሻውን ፈተና ለመቀበል በዝግጅት ላይ ያሉ ናቸው። ቀሪዎቹ ደግሞ ሥልጠናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡
አቶ ንጉሡ ጥላሁን በውይይቱ ወቅት በጀርመን ሀገር በኮንስትራክሽን ዘርፍ ሰፊ የሠራተኛ ፍላጎት ቢኖርም ጎኤቴ/ጀርመን ባህልና ቋንቋ ኢንስቲትዩት ያለው የማሠልጠን አቅም ውስን በመሆኑ ሥልጠናውን ለማስፋት ከጀርመን ኮንስትራክሽን ማኅበራት ፌደሬሽንና ከጎኤቴ/ጀርመን ባህልና ቋንቋ ኢንስቲትዩት ጋር በመነጋገር ሥልጠናው በሚሰፋበት ሁኔታ ላይ እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህንንም ለማድረግ እንደ አንድ አማራጭ የተወሰደው ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይሰጥ የነበረው የጀርመንኛ ቋንቋ ሥልጠና የተቋረጠ ስለሆነ ሥልጠናው/ትምህርቱ/ የሚቀጥልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከዩኒቨርስቲው እና ጎኤቴ/ጀርመን ባህልና ቋንቋ ኢንስቲትዩት ጋር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ሥልጠና ላይ ከሚገኙ 50 ሠልጣኞ መካከል 35ቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመገኘት አቶ ንጉሡ ጥላሁን ጋር የተወያዩ ሲሆን በሥልጠናው ሂደት፣ በምዘና ሂደቱ፣ በአሠልጣኞቹ፣ በሥልጠና ክፍያው እና በመሳሰሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ረገድ በጥንካሬ የታዩ እና መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳብ የሰጡ ሲሆን ሚንስቴር መስሪያ ቤቱም በዚህ ረገድ የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥልም ሀሳባቸውን ሰጥቷል፡፡
አቶ ንጉሡ ጥላሁንም ሥልጠናቸውን በመከታተል ያሉትን በቅርበት ክትትልና ድጋፍ የሚያደርጉላቸው መሆኑን ያነሱ ሲሆን ሁሉንም ሂደት አጠናቀው ወደ ጀርመን ለመጓዝ በዝግጀት ላይ ያሉትን በተሠማሩበት ሥራ ሁሉ በታታሪነት፣ በጥሩ ሥነምግባር እና ብቃት በመሥራት ለሀገራቸው በዘርፉ አምባሳደሮች እንዲሆኑ ከአደራ ጋር አሳስበዋል። በመንግሥት በኩልም አሰፈላጊው ክትትልና ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም አቶ ንጉሡ ጥላሁን ሥልጠናቸውንና ፈተናቸውን አጠናቀው ጀርመን ከሚገኙ አሠሪዎቻቸው ጋር የሥራ ውል የተፈራረሙት የመጀመሪያዎቹ ተጓዦች በመጪው አንድ ወር ውስጥ ጉዞ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!