“ሁሉም ወገን የመስጅዶችንና የአብያተ ክርስቲያናትን እንዲሁም የአማኞች ክብር፣ ሰላምና ደኅንነትን የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል” የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ አባቶች

119

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሁሉም ወገን የመስጅዶችንና የአብያተ ክርስቲያናትን እንዲሁም የአማናኞችን ክብር፣ ሰላምና ደኅንነትን የመጠበቅና የማስጠበቅ ሕጋዊ፣ ሃይማኖታዊና ሞራላዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ አባቶች አሳሰቡ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተከናወኑ የአርብ ስግደትን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ በተለይም በታላቁ አንዋር መስጅድ በተከሰተው ሁከትና ግጭት ምክንያት ሕይዎታቸውን ስላጡት ወገኖች የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን ብለዋል።
የሕዝበ ሙስሊሙ ልዩ ቀን በኾነው ጁምዓ ስለኾነውና በሁሉም ወገን ላይ ስለደረሰው ገዳት ሁሉ የበላይ ጠባቂ አባቶቹ ማዘናቸውንና ተግባሩንም አጥብቀው እንደሚያወግዙ ገልጠዋል::

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም በምስራቅ ጎጃምና በአርሲ አህጉረ ስብከት በሚገኙ ሁለት አጥቢያዎች ላይ ደረሰ ስለተባለው ጉዳት እየተጣራ እንደሚገኝ የቤተክርስቲያኒቱ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ የወጣው መረጃ እንደሚጠቁም በመግለጫው ተመላክቷል።

በተጨማሪም በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በሚገኙ የወንጌላውያን አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ላይ ችግሮች እንዳሉ እንገነዘባለን ብለዋል አባቶቹ።አባቶቹ በመግለጫቸው እንዳስቀመጡት መስጅዶችና አብያተ ክርስቲያናት ለአማኞቻቸው የተቀደሱ፣ ለፈጣሪም ተገቢው አምልኮ የሚፈጸምባቸው የመንፈሳዊ እና የሞራል እሴቶች የሚገነባባቸው፤ ከምእመናን ጋር ጠንካራ ስሜታዊና መንፈሳዊ ትስስር ያላቸው ናቸው ብለዋል የበላይ ጠባቂ አባቶች።

በአዲሱ የሸገር ከተማ አሥተዳደር በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መስጅዶችና አብያተ ክርስቲያናት ከሕጋዊነት ጋር በተያያዘ በመፍረሳቸው ኢትዮጵያዊያንን በተለይም ሕዝበ ሙስሊሙን አስቆጥቷል ነው ያሉት። ይህንንም ተከትሎ ግንቦት 18 እና 25 /2015 ዓ.ም በታላቁ አንዋርና ኑር መስጅዶች ተቃውሞ ለማሰማት የነበረውን እንቅስቃሴ ለማስቆም ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት በመፈጠሩ ሰዎች መሞታቸውና መጎዳታቸው ተገልጿል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሚመለከተው የመንግሥት መዋቅር ጋር የጀመረውን ውይይት መልካም ጅምር መኾኑን በመደገፍ የሚከተሉት የሰላም መልእክት እና ጥሪ አስተላልፈናል ብለዋል።

1. በሁለቱ ዓርብ ላይ በተከሰተው አሳዛኝ ክስተት በማዘን ሕግን ለማስከበርና የዜጎች ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ የተሰማራው የጸጥታ ኀይል የወሰደው እርምጃ ተገቢ አለመኾኑን በመግለፅ በጸጥታ ኀይሉ የተፈጸመውን ጥቃትን አውግዘዋል።

2. አሁንም አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች በማኅበራዊ ሚድያ አላስፈላጊ የጥላቻ ቅስቀሳና ከጉዳዩ የማይገናኝ ችግሮችን እየጎተቱ የሚያደርጉትን ቅስቀሳዎች እንዲያቆሙም አሳስበዋል።

3. የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የመጠበቅ ኀላፊነት የተጣለባቸው የመንግሥት አካላት የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት በትእግስትና በሆደ ሰፊነት እንዲያከናውኑ ተጠይቀዋል።

4. በመሪ ተቋሙ በኩል የተጀመረው ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ የማድረግ ሂደት ውጤት እስኪመጣ ሕዝበ ሙስሊሙ በትእግስት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።

5. በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥት ሥራ ኀላፊዎች የሁሉንም የሃይማኖት ተቋማት ክብርና ሰላም የመጠበቅ ሕጋዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በመግለጫው በአፅንኦት ጠይቀዋል።

6.ሁሉም ሃይማኖቶች የሚያስተምሩትን የትእግስት፣ የፍቅር፣ የይቅርታና የመከባበር የአንድነት እሴት መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo, Caamsaa 30/2015
Next article“ዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝ አስተዳደርነቱን ለመተግበር አሰራሩን እያዘመነ ነው” ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት