ኢትዮ ቴሌኮም እና የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የከተማዋን አገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

50

ባሕር ዳር: ግንቦት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮ ቴሌኮም ከአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ጋር የአዲስ አበባ ስማርት ሲቲ ፕሮጀክት አካል የኾነ የመሰረተ ልማት ግንባታ ለማካሄድ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ የተገኙት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬ ሕይወት ታምሩ ኢትዮ ቴሌኮም የከተማዋን የተለያዩ ቢሮዎችን እና አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ከዋናው የዳታ ማዕከል ጋር በቀላሉ ለማስተሳሰር እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ ይህን ሥራ ለመሥራትም የዋይድ ኤሪያ ኔትዎርክ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ይከናወናሉ ነው ያሉት፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ኢትዮ ቴሌኮም በ11 ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 44 ቢሮዎች እና የዋና ዳታ ማዕከሉ አሁን ካለው የግንኙነት ፍጥነት በማሻሻል ከፍተኛ ፍጥነት እና ጥራት ባለው የኦፕቲካል ፋይበር ግንኙነት በማስተሳሰር ለከተማ አሥተዳደሩ የሚያስረክብ መኾኑን ተናግረዋል

በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የቴክኖሎጅ ፍላጎትና የዳታ ደኅንነት ስጋቶችን ለመቅረፍ እንደሚያስችልም ነው ያብራሩት፡፡ የዋይድ ኤሪያ ኔትዎርክ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎቹ ክፍለ ከተሞችን እና ወረዳዎችን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር በተመሳሳይ ወቅት ማከናወን የሚፈልጉትን አገልግሎት ለመከወን ያስችላል ብለዋል፡፡ የአገልግሎት ሥርዓቱን በማዘመንም አስተማማኝ፣ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለነዋሪዎች ለማቅረብ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ወይዘሪት ፍሬ ሕይወት ተናግረዋል

በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ አቅም ያለው የኔትወርክ ዝርጋታ እንዲኖር በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ላይ ነን ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ ኀላፊ ሰለሞን አማረ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት ስምምነት በማድረጋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮምም በተጠበቀው ጊዜ ሠርቶ በማሰረከብ ወደ ሥራ እንዲያስገባ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ 2ሺህ 700 ዜጎች በትራፊክ አደጋ ሕይዎታቸዉ ማለፉን የመንገድ ደኅንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ።
Next articleሂዩማን ራይትስ ዎች ላወጣው ሪፖርት ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት የተሰጠ ምላሽ