
በኢትዮጵያ በተለይ ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል የሱስ ተጠቂ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ እና ሆስፒታል ወጣቱን ከሱስ በማውጣት አምራች ዜጋ ለመፍጠር አልመው በጋራ የሥነ አዕምሮ ሕክምና ሱስ ማገገሚያ ማዕከል እያስገነቡ እንደሆነ መዘገባችን የሚታወስ ነው።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የሥነ አእምሮ መምህርና የዩኒቨርስቲው የስልጠና ማዕከል አስተባባሪ መምህር አምሳሉ በለጠ ‹‹የሥነ አእምሮ በሽታ በሀገራችን በስፋት እየተከሰተ መምጣቱን ተከትሎ ከአማኑኤል እና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች ውጭ ሕክምና እየተሰጠ ባለመሆኑ ይህን ችግር ለመፍታት በክልላችን የመጀመሪያ የሆነውን ማዕከል በጋራ ገንብተናል›› ብለዋል።
የአእምሮ ሕመም ለሱስ፤ ሱስ ደግሞ ለአእምሮ ሕመም እንደሚያጋልጡ ያመለከቱት መምህሩ ሁለቱንም በጋራ ለማከም ማዕከሉ እንደተቋቋመ ገልፀዋል።
በክልሉ የችግሩን አስከፊነት ለመረዳት የተደራጀ ጥናት እንዳላደረጉ የተናገሩት መምህር አምሳሉ በአንድ ወቅት በደብረ ታቦር ሆስፒታል ኤች አይ ቪ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት 22 ነጥብ 2 ከመቶው የሥነ አእምሮ ችግር እንደገጠማቸው መታዬቱን ተናግረዋል። ነገር ግን የአእምሮ ጤና መታወክ አስከፊ እንደሆነ ለማወቅ ከጥናት ባለፈ በየአካባቢው እና በየመንገዱ ያሉ ሕመምተኞችን በማየት ምንያህል የኢትዮጵያ ችግር እንደሆነ ለመረዳት ቀላል መሆኑን ነው መምህር አምሳሉ የተናገሩት።
ከዚህ በፊት በአካባቢው የሱስ ማገገሚያ ተቋም ባለመኖሩ ከሱስ መላቀቅ የሚፈልጉ ሰዎች እድሉን ማግኘት ሳይችሉ ቆይተዋ። ማዕከሉ የሥነ አእምሮ ሕክምና መስጠት ጀምሯል፤ ከዛሬ ጀምሮ ደግሞ የሱስ ተጠቂዎችን ለማከም በዝግጅት ላይ መሆኑን መምህር አምሳሉ ተናግረዋል።
የሱስ ማገገሚያ ተቋሙ በአንድ ጊዜ 14 ሰዎችን ማስተናገድ እንደሚችል የተናገሩት መምህር አምሳሉ በሙሉ አቅሙ ሥራ ለማስጀመር ግን የሰው ኃይል እና የመድኃኒት እጥረት መኖሩን ገልፀዋል።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት አነጋግረኝ ጋሻው (ዶክተር) ደግሞ ዩኒቨርቲው ከሆስፒታሉ ጋራ በመተባበር ግብዓቶችን እያሟላ እንደሆነ ገልፀው ወደ ፊትም ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ ሥራ እንዲጀምር የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የደብረ ታቦር ጠቅላላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ገብሬ ድንቃየሁ (ዶክተር) ‹‹ሆስፒታሉ ከዚህ በፊት ሕክምናውን ባለመጀመሩ መድኃኒቶች አለመኖራቸውን ጠቁመው የሥነ አእምሮ ሐኪሞች ለሕክምና የሚያስፈልጓቸውን መድኃኒቶች ሲያቀርቡ ግብዓቱን እናሟላለን›› ብለዋል።
የሰው ኃይል እጥረት እና የአዳር ተረኞች አበል የአበል ክፍያን በተመለከተም ከክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በተደጋጋሚ ተነጋግረው ስምምነት ላይ በመድረሳቸው በቅርቡ ችግሩ ሊፈታ እንደሚችልም ገልፀዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ለአብመድ እንደተናገሩት በክልሉ ውስጥ በሚገኙ 79 ሆስፒታሎች የጥናት ቡድን በመላክ ጥናት ስለተደረገ የሥራ ጫናውን ግምት ውስጥ በማስገባት የሚቀነሰውን እና የሚጨመረውን ከለዩ በኋላ በቅርቡ ችግሩ እንደሚፈታ አመልክተዋል።
ዘጋቢ፦ አማረ ሊቁ- ከደብረ ታቦር