ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ 2ሺህ 700 ዜጎች በትራፊክ አደጋ ሕይዎታቸዉ ማለፉን የመንገድ ደኅንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ።

56

አዲስ አበባ፡ ግንቦት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመንገድ ደኅንነት እና መድን ፈንድ ለ3ተኛ ጊዜ የሚያካሂደዉን የተቀናጀ ሀገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ማስጀመሪያ መድረክን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የመንገድ ደኅንነት ጉዳይ ለአንድ አካል የሚሰጥ ሳይኾን ሁሉም በጋራ ሊሠራበት የሚገባ ነዉ ሲሉ የመንገድ ደኅንነት እና መድን ፈንድ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጀማል አባሶ ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አሥፈጻሚዉ መንግሥት የመንገድ ደኅንነትን ለማረጋገጥ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዉ ተቋሙ በ2014 ዓ.ም እንደ አዲስ ተቋቁሞ አደጋ ከመድረሱ በፊት መከላከል እና ከተከሰተ በኋላም አስቸኳይ መፍትሄ በመስጠት ሥራዎችን ሲያከናዉን እንደቆየ አስረድተዋል።

ባለፉት 9 ወራትም ለ46 ሚሊዮን ሕዝብ ስለ መንገድ ደኅንነት ግንዛቤ ተሰጥቷል ብለዋል። የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ እንደተሠራ አስገንዝበዋል።

በበጀት ዓመቱ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ከሕግ ጥሰት የተገኘ ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ እንደተደረገም ነው የገለጹት።

ዋና ሥራ አሥፈጻሚዉ በመግለጫቸዉ የትራፊክ አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመምጣቱም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ወደ 2ሺህ 700 ሰዎች በመኪና አደጋ ሕይዎታቸዉ ሲያልፍ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ንብረት ወድሟልም ብለዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ለ3ተኛ ጊዜ በተቋቋመዉ ግብረ ኀይል የግንዛቤ እና ቁጥጥር ሥራ ይሠራልም ነዉ ያሉት። ግብረ ኀይሉ የፌዴራል ፖሊስን ጨምሮ የጸጥታ አካላትን ያካተተ ነዉም ተብሏል። ከግንቦት 30/2015 ዓ.ም እስከ ሰኔ 25/2015 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በሸገር 5ቱም መዉጫዎች እና በክልሎች ደግሞ አደጋ በሚመዛባቸዉ አካባቢዎች በግብረ ኀይሉ ሥራዎች እንደሚሠሩ አንስተዋል።

ዋና ሥራ አሥፈጻሚዉ የመንግሥት ተቋማት አሽከርካሪዎች እና ተሽከርካሪዎች ደኅንነታቸዉ የተጠበቀ መኾኑን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ ኤልሳ ጉኡሽ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት የፌደራል መንግሥትን የ2016 ረቂቅ በጀት 801 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር እንዲኾን ውሳኔ አሳለፈ።
Next articleኢትዮ ቴሌኮም እና የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የከተማዋን አገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።