
‹‹ የብልጽግና ፓርቲ የፋኖን፣የቄሮን፣ የዘርማንና ሌሎች ወጣት አደረጃጀቶች በጋራ ያደረጉትን ትግል ከተረት ተረት ወደ እውነተኛ ብልጽግና ሰላም፣ ዲሞክራሲና አንድነት ለማሻጋገር የተደረገ ሂደት መሆኑ መታመን አለበት›› ኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህመድ (ዶክተር)
የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህመድ የብልጽግና ፓርቲን በተመለከተ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ውህድ ፓርቲውን በየደረጃቸው የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች ሲወያዩበት እንደቆዩ የተናገሩት ጠቅላ ሚኒስቴር ዶክተር ዐብይ ትናንት ህዳር 17/2012ዓ.ም የአማራ ዴሞክራሲያዊና ፓርቲ (አዴፓ) እና የኦሮሚያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፒ) ውህድ ፓርቲውን በሙሉ ድምጽ ማጸድቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ዴህዴን) ውህደቱን እንደሚያጸድቀው ይጠበቃልም ብለዋል፡፡ የፓርቲ ምስረታው ሁሉንም ህጋዊ መሰረት የያዘና ህግን ተከትሎ የተፈጸመ ነውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራሙን እያሻሻለ ለሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያን ወደብልጽግና ጎዳና የሚወስደውን ዕቅድ የነደፈ ይህንንም ከመላው ህዝብና አባላት ጋር የሚወያይበትና የሚያዳብረው ኢትዮጵያን ወደብልጽግና የምንወስድበትን ህልማችን እውን የምናደርግበት ትክክለኛው መንገድ የተጀመረ ነውም ብለዋል፡፡
“አንዳንድ ሐይሎች አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ አህዳዊ ስርዓትን የሚያመጣ የፌደራል ስርዓትን የሚያጠፋ የሚል አሉባልታ ሲናገሩ ይደመጣል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሮግራማችን ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የብልጽግና ፓርቲ ህብረ ብሔራዊት፣ ፌደራላዊትና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሚታጠናክርና የሚገነባ እንጂ የማያፈርስ መሆኑን በንግግር ብቻ ሳይሆን በፕሮግራማችን ጭምር አካተነዋል ብለዋል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎች ብልጽግና ፓርቲን በመክሰስ ሳይሆን አማራጭ ሀሳብ በማምጣት እንዲሞግቱና ለኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ ሃሳብ ይዘው እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የፋኖን፣ የቄሮን፣ የዘርማንና ሌሎች ወጣት አደረጃጀቶች በጋራ ያደረጉትን ትግል ከተረት ተረት ወደ እውነተኛ ብልጽግና ሰላም፣ ዲሞክራሲና አንድነት ለማሻጋገር የተደረገ ሂደት መሆኑ መታመን አለበትም ብለዋል፡፡ ፋኖ፣ ቄሮችና ሌሎች የወጣት አደረጃጀቶችም የታገላችሁለት ፓርቲ ስለተመሰረተ እንኳን ደስ ያላች ያሉት ዶክተር ዐብይ ከፓርቲያችሁ ጋር ሆናችሁ ስታነሱት የነበረውን ጥያቄ በተግባር እንዲመለስ አስፈላጊውን ጥረት እንድታደርጉ ጥሪ አቀርባለሁም ብለዋል፡፡
ድርጅቱ የፋኖንና የቄሮን ትግል የሚያስታውስና የተግባር ማስታወሻ ያስቀምጣልም ብለዋል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ አባለት በሰሞኑ ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ውስጥ የህግ ልዕልና ለማረጋገጥና ህግ የማስከበር ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ተነስቷልም ብለዋል፡፡ ከእንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብ ያለው ሰው በሃሳብ ልዕልና ስልጣን ከመያዝ ውጭ በሀይልና ትክክል ባልሆነ መንገድ የህዝብን ሰላም የሚያውክ ከሆነ መንግስት ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ የህግ ልዕልናን እንደሚያረጋግጥ እና ፓርቲው ለህግ ልዕልና አበክሮ እንደሚሰራም ተግባብተናል ነው ያሉት፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ያለብንን ድህነት ፣የዲሞክራሲ እጥረትና የሰላም ችግር በመፍታት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ስራ እንዲያገኝ፣ በልቶ እንዲያድርና በሰላም ወጥቶ እንዲገባ የሚተጋ ነው ብለዋል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ ለሰላም፣ ለእኩልነት፣ ለነጻነት፣ ለእውነተኛ የፌደራል ስርዓት፣ ለእያንዳንዱ ዜጋ በልቶ የሚያድርበት፣ ወጥቶ የመግባት ሰላምን ለማረጋገጥና ለመፈጸም ታጥቆ የተነሳ ነው ብለዋል፡፡ ፓርቲው ግልጽ ፕሮግራም ያለው፣ መጻዩን የኢትዮጵያን አቅጣጫ የነደፈ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ