የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ፈጣን፣ ፍትሐዊ እና ከሕገ ወጦች የጸዳ እንዲኾን እየሠራ መኾኑን ገለጸ።

121

👉የአፈር ማዳበሪያ ላይ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥነት ጨምሮ አጠቃላይ የስርጭት ሂደቱን የሚከታተል ቡድን ተቋቁሟል።

ባሕር ዳር : ግንቦት 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከሀገሪቱ ዓመታዊ የሰብል ምርት ውስጥ ከ40 በመቶው በላይ በአማራ ክልል ይመረታል። የክልሉ በርካታ አካባቢዎች ትርፍ አምራቾች ናቸው። ታታሪ አርሶ አደሮች ከራሳቸው ጉርስ ተርፈው ገበያውን በማጥገብ ሀገር ይመግባሉ። ይህ እንዲሆን ደግሞ የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ እና በሚፈለገው መጠን በአርሶ አደሮች እጅ መገኘት ግድ ይላል። ግብዓቶች ካልተሟሉ ታርሶ የለሰለሰው ማሳ ጦም ማደሩ፤ የገበሬው ጎተራ መጉደሉ፤ ገበያውም መራቡ አይቀሬ ነው።

ከግብዓቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የአፈር ማዳበሪያ ነው። በተለይም በ2015/ 2016 የምርት ዘመን ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በሚፈለገው ልክ ባለመሰራጨቱ አርሶ አደሮችን ስጋት ውስጥ ከትቷል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ሀይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) የአርሶ አደሮች ስጋት ትክክለኛ እና ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል። ግብርና ቢሮው ጉዳዩን በልዩ ትኩረት ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

እንደ ቢሮ ኀላፊው ገለጻ በ2015/2016 የምርት ዘመን ለአማራ ክልል ብቻ 9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተጠይቆ ነበር። ከዚህ ውስጥ ግዥ የተፈጸመው 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነው። በዚህ መጠን ግዥ ቢፈጸምም ሁሉንም ማዳበሪያ በወቅቱ ወደ ሀገር የማጓጓዙ ሥራ በመዘግየቱ እና የተጓጓዘውንም ቢሆን በፍጥነት ለአርሶ አደሮች ማከፋፈል አለመቻሉ የቅሬታ ምንጭ ሆኗል ነው ያሉት ኀላፊው።

እንደ ቢሮ ኀላፊው ገለጻ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀደም ሲል ወደ ክልሉ ገብቷል። 4 መቶ ኩንታል የከረመ የአፈር ማዳበሪያ እንደነበርም ተናግረዋል። በአጠቃላይ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ዝግጁ ነው ብለዋል።

የአፈር ማዳበሪያ ራሱን የቻለ ሕጋዊ የስርጭት ሰንሰለት አለው። ይሁን እንጅ ከተፈቀደው ሰንሰለት በማስወጣት በሕገ ወጥነት የተሰማሩ አካላት የአፈር ማዳበሪያን በእጃቸው ውስጥ አስገብተው በውድ ዋጋ እንደሚሸጡ አርሶ አደሮች ይናገራሉ። ዶክተር ሀይለማርያም አርሶ አደሮች በሕጋዊ መንገድ የቀረበላቸውን የአፈር ማዳበሪያ ከነጣቂ ሕገ ወጦች በውድ ዋጋ መግዛት እንደሌለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል። ይልቁንም አርሶ አደሮች የተቀናጀ ትግል በማድረግ እና በመጠቆም እንዲህ ዓይነት የሕገ ወጥነት ምንጮችን ማድረቅ ይገባቸዋል ነው ያሉት።

በአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ላይ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥነት ጨምሮ አጠቃላይ ስርጭቱን የሚከታተል ቡድን በቅርብ ስለመቋቋሙ ዶክተር ሀይለማርያም ተናግረዋል። ቡድኑ ከፌደራል እስከ ክልል ያሉ የተለያዩ ተቋማትን አካትቶ የተቋቋመ ሲኾን እስከ ቀበሌዎች ድረስ ወርዶ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭትን እየተከታተለ እና ክፍተቶችን እየተመለከተ ለመሙላት በመሥራት ላይ ይገኛል።

ቡድኑ ከተመለከታቸው ክፍተቶች ውስጥ በየቀበሌዎች መሰረታዊ የሕብረት ሥራ ማኅበራት እጅ የተከማቸውን ማዳበሪያ በፍጥነት ለአርሶ አደሮች ማከፋፈል አለመቻሉ አንዱ ነው። ይህ ችግር ለሁሉም አርሶ አደሮች የሚበቃ ማዳበሪያ እስከሚገኝ ድረስ ያለውንም ማሰራጨት አለመቻል ከቀበሌ አመራሮች አሠራር የመነጨ ነው ብለዋል ቢሮ ኀላፊው።

ይህ አሠራር መስተካከል እንዳለበትም ጠቁመዋል። ወደ መሰረታዊ ሕብረት ሥራ ማኅበራት የገባውን ማዳበሪያ ቅድሚያ ከአርሶ አደሮች ጋር ውይይት በማድረግ ወዲያውኑ ማከፋፈል እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቢሮው የአፈር ማዳበሪያ ችግርን ለመቅረፍ የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀመ እንደሚገኝም ኀላፊው ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ማዕከላዊ መጋዝን 150 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በብድር መልኩ በማቅረብ እየተሰራጨ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በዚህ ሳምንትም ወደብ ላይ የደረሰ 350 ሽህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ እየተጓጓዘ ነው ብለዋል።

ይህ የአፈር ማዳበሪያ እንደደረሰ ቀድመው ለሚዘሩ አካባቢዎች በፍጥነት ይሰራጫል ነው ያሉት።

ለክልሉ የተገዛው የአፈር ማዳበሪያ በሙሉ ፈጥኖ ወደ ክልሉ እንዲገባና ሁሉም አርሶ አደሮች በቂ የአፈር ማዳበሪያ እንዲያገኙ በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። በመኾኑም አርሶ አደሮች በተፈጠረባቸው ስጋት ሳይረበሹ፤ ይልቁንም እየተወያዩ እንደሚዘሩት የሰብል ዓይነት እና ወቅት ቅድሚያ ለሚዘራ ቅድሚያ እየሠጡ ያለውን እና የሚመጣውን የአፈር ማዳበሪያ በሕጋዊ መንገድ መከፋፈል እንዲችሉ ዶክተር ሀይለማርያም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያውያን አትሌቶች በስዊድን ስቶክሆልም ማራቶን ድል ቀናቸው፡፡
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት የፌደራል መንግሥትን የ2016 ረቂቅ በጀት 801 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር እንዲኾን ውሳኔ አሳለፈ።