የተማሪዎችንና የመምህራንን የፈጠራ አቅም ለማሳደግ የሙያ ትምህርት መለማመጃ ማዕከላት በትምህርት ቤቶች እንዲጠናከሩ ተጠየቀ፡፡

106

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በተማሪዎችና መምህራን የተሠሩ የፈጠራ ሥራዎችን የሚያሳይ ክልል አቀፍ አውደ ርዕይ ለሦስት ቀናት በባሕር ዳር ተካሂዷል፡፡

በአውደ ርዕዩ 140 ተማሪዎችና መምህራን ተወዳድረው በቀጣይ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሳተፉ አሸናፊዎች ተለይተዋል፡፡ ለአሸናፊዎችም የእውቅና ሥነ ሥርዓትም ተካሂዷል፡፡

አሸናፊ ከኾኑት መካከል ከሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ እነዋሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ዳዊት አድማሱ አንዱ ነው፡፡ ተማሪ ዳዊት ሽልማቱን ያገኘው በሠራው የፈጣን ኀይል ቆጣቢ ኤሌክትሪክ ምጣድ ነው። ምጣዱ ከኤሌክትሪክ በተጨማሪ በሲሊንደር፣ በሶላር፣ በባዮ ጋዝ፣ በእንጨትና በከሰል የኀይል አማራጮች እንደሚሠራ ነው የነገረን፡፡ ይህም ከከተሞች ውጭ በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል በጭስ የሚሰቃዩ እናቶች በአካባቢያቸው ያለውን የኀይል አማራጭ እንዲጠቀሙ ያስችላል፡፡

ተማሪ ዳዊት እንዳለው አሁን ላይ በኤሌክትሪክ አገልግሎት እየሰጠ ከሚገኘው ምጣድ አንድ እንጀራ ለማውጣት ሦስት ደቂቃ ይወስዳል፤ ይህንንም በፈጠራ በተገኘው ምጣድ ወደ 1 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። ይህ ደግሞ የኤሌክትሪክ ፍጆታን 50 በመቶ ይቀንሳል፡፡ የፈጠራ ሥራው ፈጣን በመኾኑ ጊዜ ቆጣቢ ያደርገዋል፡፡ ድንገት አገልግሎት እየሠጠ የኤሌክትሪክ ኀይል ቢቋረጥ እስከ ሦስት እንጀራ የመጋግር ኀይል የመያዝ አቅም እንዳለውም ነግሮናል፡፡

የፈጠራ ባለቤቱ እንዳለው በአካባቢው በኤሌክትሪክ ኀይል መቆራረጥ ምክንያት እናቶች ሲቸገሩ በመመልከቱ የፈጠራ ሥራውን ለመሥራት እንዲነሳሳ አድርጎታል፡፡ ለሥራው ደግሞ በአካባቢው የወዳደቁ ብረታብረቶችን በመሰብሰብ መጠቀሙን ነው የነገረን፡፡

በትምህርት ቤቱ በገንዘብና በቁሳቁስ አቅርቦት ችግር አቅማቸውን ማሳየት ያልቻሉ አቅም ያላቸው ተማሪዎች እንዳሉም ነግሮናል፡፡ በቀጣይ ትምህርት ቤቶች ከንድፈ ሃሳብ ትምህርት ባለፈ ተግባር ተኮር ትምህርት ላይ ትኩረት መሰጠት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቤተ ሙከራዎችንና የፈጠራ አቅምን የሚያጎለብቱ የሙያ ትምህርት መለማመጃ ማዕከላትን ማጠናከር እንደሚገባ አንስቷል፡፡

ወጣቱ አሁን ያቀረበውን ፈጠራ በማሻሻል በቀጣይ ዓመት በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ውድድር ለማሸነፍ እንደሚሠራ ገልጾልናል፡፡ ከአስር በላይ ፈጠራዎች እንዳሉት ያነሳው ተማሪ ዳዊት በቀጣይ እነዚህን የፈጠራ ውጤቶች በማሳደግ የግዙፍ ድርጅት ባለቤት የመኾን ሕልም እንዳለው ነገሮናል፡፡

የተማሪ ዳዊትን የፈጠራ ውጤት ለአብነት ጠቀስን እንጅ ሌሎችም ተማሪዎች እና መምህራን ባቀረቡት የፈጠራ ሥራ ተሸላሚ ኾነዋል፡፡ አሸናፊዎች በቀጣይ በሚዘጋጀው ሀገራዊ የፈጠራ ሥራ ውድድር የሚሳተፉ ይኾናል፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እየሩስ መንግሥቱ እንዳሉት፤ በመምህራን እና በተማሪዎች የታየው የፈጠራ ውጤት ከትምህርት ሴክተሩ ድጋፍ በተጨማሪ በተማሪዎችና በመምህራን ጥረት ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች የፈጠራ ማእከል እንዲኾኑ ከተፈለገ የትምህርት ተቋማት ከሚያደርጉት ድጋፍ ባለፈ ወላጆች፣ ባለሃብቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና አጋር አካላት እንዲደግፉ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሥራቸው ተወዳድረው አሸናፊ የኾኑ የፈጠራ ሙያተኞች በፌዴራል ደረጃ የሚሸለሙበት ውድድር ሊካሄድ መኾኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
Next articleኢትዮጵያውያን አትሌቶች በስዊድን ስቶክሆልም ማራቶን ድል ቀናቸው፡፡