
አዲስ አበባ: ግንቦት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ማሰልጠን፣ መሸለም ፣ ማብቃት በሚል መርህ የሚያካሂደው እና በሁሉም ክልሎች ከወረዳ ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ብሩህ ሀገር አቀፍ የንግድ ሥራ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር ከ200 የክልል ተወዳዳሪዎች አሸናፊዎቹን የሚለይበት መርሐ ግብር በቡራዩ የተሰጥኦ ልማት ትምህርት ቤት ተጀምሯል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን “ብሩህ” የተሰኘው መርሃ ግብር እንዲህ አይነት ከማኅበረሰቡ የሚመነጩ አቅሞችንና ፈጠራዎችን ለማጎልበት የተጀመረ ነው ብለዋል።
በየአካባቢው በርካታ የተለያዩ ፀጋና አቅሞች አሉን ያሉት አቶ ንጉሱ ሃሳቦች ከተፈጠሩ በኋላ ወደ ተግባር መለወጥ እንዲችሉ እንዲህ አይነት ተግባራትን ማጠናከርና ማጎልበት ያስፈልጋል ብለዋል። በ2013 ዓ.ም የተጀመረው የፈጠራ ሥራ ውድድር በዚህ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ሲኾን ከየክልሎቹ የተመዘገቡት 1ሺህ 16 የፈጠራ ሃሳቦች ሲኾኑ ከዩኒቨርሲቲዎች 127 መመዝገባቸው ተገልጿል።
ለውድድሩ የመመልመያ መስፈርትና ፎርማቶችን በማዘጋጀት ለ1ሺህ 240 ወረዳዎች፣ ለ98 ዞኖች፣ ለፖሊቴክኒክ ኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲዎች በየክልሎቹ አማካኝነት እንዲሰራጭ መደረጉ ተገልጿል።
ውድድሩ ይፋ ከተደረገበት እስከ ሚያዚያ 15/2015 ዓ.ም ድረስ ከተማ አሥተዳደሮች እና ክልሎች ከወረዳ ጀምረው አወዳድረው የተሻለ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን በማበረታታት በፌዴራል ደረጃ ለሚካሄደው ውድድር ዝግጁ ካደረጉ በኋላ ከየክልሉ ያለፉት 200 ተወዳዳሪዎች ከግንቦት 28/2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተዘጋጀላቸው ቡራዩ ተሰጥዖ ማበልፀጊያ ትምህርት ቤት የማሰልጠኛ ካምፕ ገብተዋል ተብሏል።
በቆይታቸውም የሥራ ፈጠራ ሃሳብን ወደ ተግባር መቀየር እና የንግድ አመሰራረትን በተመለከተ ስልጠና ይሰጣቸዋል ተብሏል።
ከተወዳዳሪዎቹ መካከል በየደረጃው ተወዳድረው አሸናፊ የሚኾኑትን 50 ምርጥ ሀሳቦች በፌዴራል ደረጃ በመሸለም ብሩህ ኢትዮጵያ 2015 ውድድር የሚጠናቀቅ ይኾናል። እስካሁን በተካሄዱ 7 ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ ውድድሮች በአጠቃላይ 2ሺህ 412 አመልካቾች የተሳተፉ ሲኾን ለ400 ሃሳብ ባለቤቶች ወይም 552 ወጣቶች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በአጠቃላይ ለ167 ምርጥ ሃሳቦች የ1ሚሊዮን 518 ሺህ ዶላር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል ብለዋል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታው ንጉሱ ጥላሁን።
ብሩህ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሀሳቦች ውድድር ፕሮግራም በኢትዮጵያ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ ቁልፍ ችግሮችን ለመፍታትና የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚችሉ አዳዲስ ሀሳቦች ይዘው የሚመጡ ወጣቶችን ለማበረታታት የተዘጋጀ የውድድር መርሃ ግብር መኾኑ ተነግሯል።
ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!