
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በሕዝብ ብዛት ተመስርቶ ለሚደረገው ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል፣ ለውሳኔ ሰጪው እና ፖሊሲ አውጭው የመረጃ ምንጭ ኾኖ ያገለግላል፡፡ በክልሉ የሚኖረውን ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻ እና መሰል ኩነቶችን ተከታትሎ መመዝገብ በመረጃ ላይ ለተመሰረተ አገልግሎት አስፈላጊ ነው፡፡
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት በበጀት ዓመቱ 500 ሺህ 82 ሁነቶችን ለመመዝገብ አቅዶ ነበር ያሉን የአገልግሎት ሕዝብ ግንኙነት ኅላፊ ወይዘሮ ማስተዋል አለባቸው ባለፉት 9 ወራት 344 ሺህ 583 ኩነቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡ የእቅድ አፈጻጸሙ 70 በመቶ መኾኑንም የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊዋ ገልጸዋል፡፡ ለተለያዩ አገልግሎቶች ሲባል ወቅት ያለፈባቸው ምዝገባዎች በብዛት ይካሄዳሉ ያሉት ወይዘሮ ማስተዋል እነዚህ ወቅት ያለፈባቸው ምዝገባዎችን ጨምሮ 107 በመቶ መፈጸም ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ለተገኘው አፈጻጸም መሳካት የተቋማት አብሮ የመሥራ ባሕል ማደግ፣ በየደረጃው ግንዛቤ መፈጠሩ እና የሥራ አመራሩ ጉዳዩን በባለቤትነት ይዘው መሥራታቸው ነው የሚሉት ወይዘሮ ማስተዋል የክልሉ ሕዝብ ኩነቶችን ማስመዝገብ እንደሚጠበቅበት ተረድቶ ለበለጠ ስኬት አብሮ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
እስካሁን ባለው የተቋሙ የሥራ አፈጻጸም ሂደት ላይ ለላቀ ስኬት ማነቆ የኾኑ አሠራሮች እና ደንቦች እንዲሻሻሉ ተለይተው ለክልሉ መንግሥት ቀርበዋል ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊዋ አደረጃጀቱ ሲሻሻል እና ማነቆ የኾኑ የአሠራር ሂደቶች ሲፈቱ ከአሁኑ የተሻለ ውጤት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ወይዘሮ ማስተዋል የወሳኝ ኩነቶችን ምዝገባ ማንዋል ከኾነው ሥርዓት አውጥቶ ዲጂታል ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ መኾኑን አንስተው እስካሁን ባለው ሂደት ከ300 በላይ ቀበሌዎች ምዝገባቸውን በዲጂታል እያካሄዱ ነው ብለዋል፡፡ የክልሉን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ለማድረግ በቂ የመሠረተ ልማት እና ግብዓት አቅም ስለሚጠይቅ እሱ እስኪሟላ ድረስ ወሳኝ የኾነው የምዝገባ ሂደት በነበረበት አጠናክሮ ማስቀጠል ከምንም በላይ የሚጠቅመው ክልሉን ነው ብለዋል፡፡
ኩነቶችን በወቅቱ ማስመዝገብ መብት ብቻ ሳይኾን ግዴታም ጭምር መኾኑን በማወቅ ዜጎች ሁነቶችን በወቅቱ እንዲያስመዘግቡም ጥሪ ቀርቧል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች በጤና ተቋማት የአንድ መስኮት አገልግሎት የልደት ምዝገባ እየተካሄደ መኾኑን ያነሱት የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊዋ ትምህርት ቤቶችም አዲስ ገቢ ተማሪዎች የልደት ካርድ የምስክር ወረቀት ይዘው እንዲቀርቡ እያደረጉ መኾኑን አንስተዋል፡፡ እነዚህን ተሞክሮዎች በማስፋት ሁሉም ዜጋ እና ተቋማት ኅላፊነታቸውን እንዲወጡ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!