“የኮንስትራክሽን ዘርፉን የሚመጥን የአሠራር ሥርዓትን መዘርጋት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ኾኗል” የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር

96

አዲስ አበባ: ግንቦት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ አሠራርን ለማሻሻል የሚረዱና ለፖሊሲ ምክረ ሃሳብ የሚሰጡ የጥናት ሰነዶች ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች፣ የሴክተር ተቋማት ኀላፊዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የፖሊሲ አውጪዎች፣ ህንጻ ተቋራጮች፣ የሪል እስቴት አልሚዎች፣ አማካሪ ድርጅቶች፣ የግንባታ ግብዓት አምራቾች፣ የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አባላት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎች፣ አጋር የሚዲያ አካላት፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባልደረቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ምክክር እየተካሄደ ነው።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ መድረኩ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከናወነው የቢግ 5 ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚዬም መድረክ ይዞት የመጣውን ድል በአግባቡ ለመጠቀም በምንችልበት ሁኔታ ውስጥ ኾነን የምናካሂደው በመኾኑ እንደ ጥሩ አጋጣሚ የሚቆጠር ነው ብለዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አሁናዊ ሁኔታ ሲቃኝ በሀገሪቱ የሚገኙ በርካታ የገጠር አካባቢዎች ወደ ከተማነት እያደጉ የመጡ በመኾናቸው የኮንስትራክሽን ዘርፉን ከፊት ኾኖ ለመምራት የዘርፉን ዕድገት የሚመጥን የአሠራር ሥርዓትን መዘርጋት ውቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ኾኗል ነው ያሉት።

መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ አደረጃጀቶችና አሠራሮችን በመዘርጋት የዘርፉ ተዋናዮችን አቅም ለማሳደግና ያላቸውን አስተዋፅኦ ከፍ በማድረግ በዘርፉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ለዘርፉ ተዋናዮች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ ይኛል ብለዋል ሚኒስትር ደኤታው።

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከልማት ዘርፎች ፊት እየቀደመ የሚመራ ታላቅ ዘርፍ እንደመኾኑ መጠን በኢትዮጵያ ሀገራዊ የልማት ፍላጎትና ዕድገት ላይ የራሱን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ የሚገኝ ቢኾም በዚህ የዕድገት ማዕቀፍ ውስጥ ኾኖ በውስብስብ ችግሮች እየተፈተነ ያለ ዘርፍ ነው።

ያለበትን ውስብስብ ችግር በመፍታት ለሚጠበቀው ውጤት እንዲበቃ ለማድረግና በውጤታማነት ለማስቀጠል ችግሩ በአንድ ተቋም ጥረት ብቻ የሚፈታ ባለመኾኑ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላት፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ የዘርፉ ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች እና ግለሰቦች፣ አማካሪዎች፣ ተቋራጮች፣ የሙያ ማኅበራት፣ የግንባታ እቃ አምራቾች እና አቅራቢዎች፣ የፋይናንስ እና የግብይት ተቋማት በአጠቃላይ የሁሉም የባለድርሻ አካላት ውህደት እና ርብርብ የሚጠይቅ ስለኾነ ለግንባታ ፕሮጀክቶች ስኬት የሁሉም ቅንጅት መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።

የተዘጋጁ የጥናት ሰነዶች ለዘርፉ ባለድርሻ አካላት ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ሲኾን በቀጣይም የሚሰጡ ግብዓቶችን በማካተት ተሳታፊ አካላት የድርሻቸውን ወስደው እንዲተገብሯቸው ይደረጋል ተብሏል።

የመድረኩ መዘጋጀት ዋነኛ ዓላማም ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዉ የሚያስፈልጉ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች አቅርቦትን ለማሻሻል፣ ቀጣይነት ያለው የአቅርቦት ሰንሰለትን ለመፍጠር፣ ለኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና የመሳሪያዎች አቅርቦት የፋይናንስ ድጋፍን ለማመቻቸት፣ በዚህ መድረክ ተሳታፊ ከኾኑት ጋር ለቀጣይ ሥራዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እና በተዘጋጀው የመነሻ ጥናት ሰነድ ላይ ለመመካከር ሲኾን ተሳታፊዎች የድርሻቸውን በመውሰድ ወደ ተግባር የሚገቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸትም ነው፡፡

ዘርፉ ለመንግሥትና ለኅብረተሰቡ የልማት ፍላጎት የተሳካ ምላሽ መስጠት በሚችልበት ቁመና ላይ እንዲገኝ የጋራ ርብርብ እንዲደረግ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባለፉት 9 ወራት የእቅዱን 70 በመቶ ወሳኝ ኩነቶችን መመዝገቡን የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
Next articleበሥራቸው ተወዳድረው አሸናፊ የኾኑ የፈጠራ ሙያተኞች በፌዴራል ደረጃ የሚሸለሙበት ውድድር ሊካሄድ መኾኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡