
ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ለዘንድሮው የመኸር ምርት ዘመን ጥቅም ላይ የሚውል በዓይነትና በብዛት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ነው ቢሮው ያስታወቀው።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ እየገጠመ ያለውን የሰውሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ችግር ከመፍታትም ባሻገር ዘላቂ የአፈር ለምነትን ለማስጠበቅ የሚያስችል ስለመኾኑ ነው ባለሙያዎች የሚያስረዱት።
እናም በአማራ ክልል ዘርፈብዙ ጠቀሜታ ያለውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ተብሏል።
የአፈር ለምነትን መጠበቅ በሚያስችለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቃሚነት ላይ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መኾኑን የምእራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ጥላሁን አለምነህ ለአሚኮ ተናግረዋል።
በዞኑ በተያዘው የምኸር የምርት ዘመን ጥቅም ላይ የሚውል ከ10 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ኮንፖስት እንደተዘጋጀም ነው የተናገሩት። ትርፍ አምራች የኾነው ምእራብ ጎጃም ዞን በየጊዜው በሚገጥመው የሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ችግር እየተፈተነ መኾኑን ያስረዱት ኀላፊው ሌሎች አማራጮችን እየተጠቀሙ ለተሻለ ምርታማነት ለመብቃት መትጋት ግን የግድ ኾኗል ነው ያሉት።
በተመሳሳይ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ወደ እርሻ ማሳው እየቀላቀሉ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ አስፋው (ዶ.ር) ናቸው። ኀላፊው እንዳሉት በራስ አቅም ከአካባቢ የሚዘጋጅ፣ አንዴ ተጠቅሞ ለተከታታይ ዓመታት የአፈር ለምነትን የሚያሳድግ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ የኾነውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት ለዘላቂው የግብርና እድገት ባሕል ማድረግ ይገባል።
ለውጤታማነቱም ለአርሶ አደሮች ከግንዛቤ ማሳደግ እስከ ሙያዊ አዘገጃጀት በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በአማራ ክልል የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ መጠቀም ልምድና ተጠቃሚነት እያደገ መኾኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው ተናግረዋል።
ለተያዘው የምኸር ምርት ከ77 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ኮንፖስት ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ብለዋል አቶ አጀበ።
በክልሉ አሲዳማ አፈርን ማከም፣ ህያው ማዳበሪያ፣ ባዩ ሳላሪ፣ አረንጓዴ ማዳበሪያ፣ መደበኛ ኮንፖስትን በመጠቀም ለምርታማነት ትኩረት እንደተሰጠውም ተገልጿል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!