
በ193 ሚሊዮን ብር የሚገነባው የደብረ ታቦር የባሕል ማዕከል ወደ ግንባታ ለመግባት ከታቀደለት ከ282 ቀናት መዘግዬት በኋላ ተጀምራል። ግንባታውን በሦስት ዓመታት ውስጥ አጠናቅቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ቢታሰብም በተለያዩ ምክንያቶች በተቀመጠለት ጊዜ ወደ ግንባታ ሳይገባ መቆየቱን የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳድር ባሕል፣ ቱሪዝም ስፖርት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ደብረ ታቦር እና አካባቢው ለረጅም ጊዜ ፖለቲካዊ መስተጋብሮች ተከውነውበታል። አካባቢው የበርካታ ባሕላዊ እሴቶች ባለቤት እንደሆነ የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳድር የባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የባሕል እሴቶች ልማት ባለሙያ አቶ በላይ ኃይለማሪያም ተናግረዋል። ቡሄ፣ አሸንድዬ፣ የሆሳዕና መንፈሳዊ እና ባሕላዊ በዓል፣ በየዓመቱ ጥር 25 የሚከበረው የፈረስ ጉግስ፣ የገና ጨዋታ፣ ትግል፣ ገበጣ እና ሌሎች ባሕላዊ ጨዋታዎች በዞኑ የሚታወቁ ባሕላዊ እሴቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ዓፄ ቴዎድሮስ ያሠሩት ሴቫስቶፖል መድፍ፣ የተለያዩ ነገሥታት አልባሳት፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ አለባበስ፣ የዓፄ ዮሐንስ 4ኛ ቤተ መንግሥት፣ የበርካታ ጥንታዊ ገዳማት እና የባሕላዊ እሴቶች ባለቤት ቢሆንም ትኩረት ባለመሰጠቱ አካባቢው ተጠቃሚ አለመሆኑን ነው ባለሙያው የገለጹት።
እነዚህን ታሪካዊ እና ባሕላዊ እሴቶች በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ጥናት እና ምርምሮች እንዲካሄዱ፣ በተደረጃ አግባብ ንዲጎበኙ በማድረግ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በደብረ ታቦር ከተማ የባሕል ማዕከል ግንባታ ተጀምሯል።
ይሁን እንጅ የግንባታ ቦታው ከሦስተኛ ወገን ነፃ ባለመሆኑ እና ቅድመ ክፍያ ባለመለቀቁ ግንባታው እንዲዘገይ ምክንያት እንደሆነ ባለሙያው ተናግረዋል።
አቶ በላይ እንዳሉት ግንባታው በ3 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ነው፤ በዚህ ወቅትም የአንዱ ብሎክ ግንባታ ሥራ 6 በመቶ ደርሷል። ለግንባታው 193 ሚሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን በሦስት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታስቦ ነበር ወደ ሥራ የተገባው።
ማዕከሉ የተለያዩ የባሕል ዕቃዎች የሚጎበኙባቸው የክምችት ክፍሎች፣ የተለያዩ መጠን ያላቸው አዳራሾች እና ቢሮዎች የሚኖሩት ባለ ሁለት፣ ባለአራት እና ባለስድስት ፎቅ ሦስት ሕንጻዎች የሚኖሩት እንደሆነም ገልጸዋል።
ደብረ ታቦር በ1327 ዓ.ም ተመሥርታ የበጌምድር እና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት ማዕከል ሆና አገልግላለች። ለ75 ዓመታት ደግሞ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እንደነበረች ከባሕል፣ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ