በምሥራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ 36 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የጠጠር መንገድ በኀብረተብ ተሳትፎ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።

116

ደብረማርቆስ: ግንቦት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመንገድ መሠረተ ልማቱ ለዘመናት የቆየውን የኀብረተሰቡን የመንገድ ችግር የፈታ ሲኾን፣ ሰባት ቀበሌዎችን ከወረዳው ከተማ ጋር ያገናኛል። በዚህም ማቻከል፣ ስናን እና ቢቡኝ ወረዳዎችን ማገናኘትም ችሏል።

የማቻከል ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ታምሩ ዘውዴ በመንግስትና በኀብረተሰቡ ተሳትፎ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃዉ 36 ኪ.ሜ የጠጠር መንገድ መገንባት አርሶ አደሮች የሚያመርቱትን ምርት በቀላሉ ለገበያ እንዲያቀርቡ ከማስቻሉም በላይ የምሥራቅ አፍሪካ የዉኃ ማማ የኾነዉን የጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የማይተካ ሚና አለዉ ብለዋል።

ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የኾነው አማሪ የወበሽ -ድንጋይ በር የጠጠር መንድ በማኀበረሰብ ተሳትፎ የተሠራ ሲኾን ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበትም ዋና አሥተዳዳሪው አስረድተዋል።

ወረዳው በተያዘው 2015 በጀት ዓመት በማኀበረሰቡ ተሳትፎና በወረዳ አሥተዳደሩ ከ67 ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገድ በመገንባት ላይ መኾኑንም ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን መንገድ መምሪያ ኃላፊ አቶ መልካሙ ሽባባው እንዳሉት የዞኑን የመንገድ ችግር ለመፍታት ኀብረተሰቡን በማስተባበር ከ181 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ ተችሏል።

በዚህም፦

✍️158 ኪሎ ሜትር አዲስ የጠጠር መንገድ
✍️750 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና
✍️69 መለስተኛ ድልድዮች እና
✍️8 ከፍተኛ ድልድዮች በመሰራት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቶ በትግሉ ተስፋሁን በክልሉ ከ541 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመው ፕሮጀክቶቹም ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ በጀት እየተገነቡ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ በክልል በጀት፣ በፌደራል መንገድ ፈንድ እና በኀብረተሰብ ተሳትፎ እየተገነቡ መኾናቸውን የተናገሩት ኀላፊው በክልሉ በኀብረተሰቡ ተሳትፎ 978 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከ181 ሚሊዮን ብር በላይ ከምሥራቅ ጎጃም ዞን የተሰበሰበ ነው ብለዋል።

የክልሉ የመንገድ ሸፋን አሁን ላይ ከ31ሺህ ኪሎ ሜትር አይበልጥም ያሉት አቶ በትግሉ በ2022 ዓ.ም ከ51 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ለማድረስ እየተሠራ ነው፤ ኀብረተሰቡም አሁን እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎችም በተለይ በክረምት ወቅት እናቶችን ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ፣ የሚያመርቱትን የግብርና ምርት ወደ ገበያ ለማቅረብ በእጅጉ ይቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል። አሁን ላይ የመንገዱ ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ከዚህ በፊት ይደርስባቸው የነበረውን እንግልትና ስቃይ በማቃለሉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በምረቃ መርኃ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎችም ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ አማረ ሊቁ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የጠገዴ ወረዳ የማክሰኞ ገበያ ነዋሪዎች የወሰንና ማንነት ጥያቄዎች በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጣቸው ለዓለም ማኅበረሰብ ድምፃቸውን አሰሙ።
Next article“ለነጻነታችን ዋጋ ከፍለንበታል ወደ ኃላ ላንመለስ ነጻ ወጥተናል” የወልቃይት ወረዳ ነዋሪዎች