
ባሕር ዳር : ግንቦት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልል አቀፍ ፈተና እና የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በ2015 ዓ.ም በአዲሱ ፍኖተ ካርታ ተቃኝቶ እንደሚሠጥ እና የ6ተኛ ክፍል ፈተና ደግሞ ለዘንድሮ ብቻ በወረዳ ደረጃ እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ፈተናው በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ ይጀመራል ቢባልም የአማራ ክልል በትምህርት ግብዓት አቅርቦት እጥረት ምክንያት የ6ኛ ክፍል ፈተና በ2015 ዓ.ም በክልል ደረጃ እንደማይሰጥ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጅ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ፈተና በአዲሱ ፍኖተ ካርታ መሠረት እንደሚሰጥ ነው ያስታወቀው።
የ6ኛ ክፍል ፈተና በክልል ደረጃ ባይሰጥም ተማሪዎች በወረዳ ደረጃ የተዘጋጁ ፈተናዎችን ለመፈተን ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን ነግረውናል፡፡
ተማሪ ሙሉነሽ አዱኛ የሽንብጥ አንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ በዚህ ዓመት በወረዳ ደረጃ ለሚሰጠው ፈተና ዝግጅት እያደረገችም እንደኾነ ነው የነገረችን። ለዚህም ተማሪ ሙሉነሽ በክፍል ከሚሰጣት ትምህርት በተጨማሪ ቤቷ ፕሮግራም አውጥታ የማንበብ ልምድ ስላላት ጥሩ ውጤት ለማምጣት ጥረት እያደረገች እንደሆነ ነግራናለች፡፡
ሌላው የዚሁ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ጌታቸው ዋሲኹን ትምህርቱን በርትቶ በማጥናት አውሮፕላን አብራሪ የመኾን ዕቅድ አለው፡፡ አንድ መጽሐፍ ለሁለት ተሠጥቷቸው እየተማሩ እንደኾነም ነው የነገረን፡፡ ክልል አቀፍ ፈተናው ቢቀርም በወረዳ ደረጃ የሚሰጠውን ፈተና በብቃት ለማለፍ መምህራን የሚሠጡትን የማበረታቻ ትምህርት በአግባቡ እየተከታተለ መኾኑንም አስረድቷል፡፡ ተማሪ ጌታቸው የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት መኖር መምህራን ጊዜያቸውን ኖት በማዘጋጀት ላይ እንዲጠመዱ አድርጓል ብሏል፡፡ “እኛም ኖት በመጻፍ ስለምንጠመድ ለመረዳዳት እና ለማጥናት ችግር ፈጥሯል” ነው ያለው፡፡
መምህርት የሽመቤት እጅጉ የሽንብጥ አንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአማርኛ መምህር ናቸው፡፡ ለተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት ፕሮግራም አውጥተው በማስተማር ከሌሎች ተማሪዎች ጋር እንዲወዳደሩ እያደረጉ ነው፡፡ ተማሪዎች ጊዜያቸውን ለጨዋታ ከማዋል ወጥተው ለጥናት እና ለመረዳዳት እንዲያደርጉ አጥብቀው ይሠራሉ፡፡ መምህርት የሽመቤት መጽሐፍ በአግባቡ ለተማሪዎች አለመዳረስ ፈተና ቢኾንም የዘመኑን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው መጽሐፉን በየክፍለ ትምህርቱ እያባዙ ለተማሪዎቻቸው በማዳረስ ተማሪዎቻቸውን እያገዙ ስለመኾኑ ነግረውናል፡፡ የተማሪዎቻቸውን የወደፊት ሕይዎት በተሻለ መንገድ ለመምራት ተግተውም እየሠራን ነው ብለዋል መምህርቷ፡፡
የሽንብጥ አንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ጋሻው ጥሩነህ የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እንደሚሰጥ መረጃ የተላለፈ ቢሆንም ዘግይቶም ቢኾን ግን የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልል አቀፍ ፈተና እንደማይወስዱ የሚገልጽ መልዕክት ደርሶናል ብለዋል፡፡ ፈተናው በክልል ደረጃ ባይሠጥም ተማሪዎችን ለወረዳ ፈተና እያዘጋጁ ነው፡፡ የተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍ እጥረት መኖሩ የመማር ማስተማር ሁኔታውን እየረበሸው ቢኾንም ትምህርት ቤቱ ከመምህራን ጋር ባደረገው መግባባት መምህራን በቀረበላቸው ቴክኖሎጅ መሠረት እያስተማሩ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡
ተማሪዎችን ተወዳዳሪ ለማድረግ እና የተማሪዎችን ራዕይ ለማሳካት እየሠሩ ነው፡፡ ተማሪዎች በመምህሮቻቸው የሚቀርብላቸውን ትምህርት በአንክሮ እንዲከታተሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ርዕሰ መምህሩ ወላጆች ለማካካሻ ትምህርት ልጆቻቸውን በአግባቡ ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ተማሪዎች ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉም አሳስበዋል፡፡በትምህርት ቤቱ እንግሊዝኛ እና አካባቢ ሳይንስ መማሪያ ማስተማሪያ መጽሐፍ ለሁለት አንድ መሠጠቱንም ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ዳይሬክተር ካሴ አባተ የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በዚህ ዓመት ሳይኾን በ2016 ዓ.ም እንደሚሠጥ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓመት በቂ መጽሐፍ ለሁሉም ተደራሽ ባለመደረጉ ክልላዊ ፈተናውን ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻል ነው ያብራሩት፡፡
በቀጣይ ዓመት የሚፈተኑ ተማሪዎች አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት እየተማሩ የቆዩ በመኾናቸው ለዝግጅት አይቸገሩም ብለዋል፡፡ አቶ ካሴ ተማሪዎችን ለሚቀጥለው ለማለማመድ ሞዴል ፈተናዎች ተዘጋጅተው እንደሚፈተኑም ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎች ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተመሳሳይ የዕውቀት ደረጃ ላይ እንዲገኙ መጽሐፍ የማሳተም ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ከነችግሩም ቢኾን በትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲው በተካተተው መሠረት በሚቀጥለው ዓመት ፈተናው ይሠጣል ብለዋል፡፡
ትምህርት ቢሮው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በ2016 ዓ.ም የሚፈተኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ፣ ወላጆች ልጆቻቸው በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የሚማሩ መኾኑን ተገንዝበው ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ መምህራንም የተማሪዎችን ችግር ተገንዝበው በቂ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!