በሀገራዊ ምክክሩ ውስጥ የአማራ ሕዝብ በተገቢዉ መንገድ እንዲወከል መሥራት እንደሚያስፈልግ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን አስታወቀ።

117

አዲስ አበባ : ግንቦት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ አብን “ሀገራዊ ምክክር የሀገራችን ሥርዓታዊ እና መዋቅራዊ ተግዳሮቶች በተለይም ከአማራ ሕዝብ አንጻር “በሚል የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ አዘጋጅቷል።

የአብን ምክትል ሊቀ መንበር አቶ መልካሙ ሹምየ የአማራን ሕዝብ ብሎም የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ በማስተናገድ ሀገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በውይይት መድረኩ ዶክተር ያሲን ሁሴን “ሀገራዊ ምክክሩ እንደ ሀገር ያለው ፋይዳ” በሚል ርዕስ ጽሑፍ አቅርበዋል። ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲኾን የፖለቲካው ኹኔታ ፣ የመንግሥት እና የልሂቃን ፈቃደኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉን አቀፍ መኾን እንዳለበት ያነሱት ዶክተር ያሲን የጋራ አቋም መያዝም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በሚሳተፉ አካላት መካከል ሰፊ የሀሳብ ልዩነት ካለ የሀገራዊ ምክክሩ እንዳይሳካ ተግዳሮት ይኾናል ብለዋል።

የአማራ ክልልም በብሔራዊ ምክክሩ በተጠናከረ መልኩ ተሳታፊ እንዲኾን የተቀናጀ ሥራ መሠራት እንዳለበት ጠቅሰዋል።

“ሀገራዊ ምክክሩ ከአማራ ሕዝብ አንጻር” በሚል ርዕስ ጹሑፍ ያቀረቡት ዶክተር ዮናስ ተስፋ በበኩላቸዉ ከዚህ በፊት በተደረጉ ምክክሮች የአማራ ሕዝብ በተገቢው መልኩ አልተወከለም ሲሉ አንስተዋል ።

አሁን ላይ በሚደረገዊ ሀገራዊ ምክክር ላይ አማራ ጠል ሀሳቦች እና ትርክቶች ላይ በስፋት በመወያየት አቋም መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል። መተማመን ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።

በምክክሩ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙ የተጠናከረ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎች ያስፈልጋሉ ተብሏል ።

ዘጋቢ :- ኤልሳ ግዑሽ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን የሚዘክር የአርኪኦሎጂና የቨርቹዋል ሪያሊቲ ቋሚ ዐውደ ርዕይ በላሊበላ ከተማ ተከፈተ።
Next articleበዚህ ዓመት በክልል አቀፍ ደረጃ ሊሰጥ የነበረው የስድስተኛ ክፍል ፈተና በወረዳ ደረጃ የሚሰጥ መሆኑን ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡