የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን የሚዘክር የአርኪኦሎጂና የቨርቹዋል ሪያሊቲ ቋሚ ዐውደ ርዕይ በላሊበላ ከተማ ተከፈተ።

88

ባሕር ዳር : ግንቦት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ላሊበላ በእምነት የታነፀ” በሚል መሪ ሀሳብ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን የሚዘክር የአርኪኦሎጂና የቨርቹዋል ሪያሊቲ የቋሚ ዐውደ ርዕይ በላሊበላ ከተማ ተከፍቷል።

በመርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፤ በቱሪስት መዳረሻ ታሪካዊ ቅርሶች ዙሪያ ዕሴት የሚጨምሩ ተግባራትን በማከናወን ተወዳዳሪ መዳረሻነትና ማኅበራዊ አቀፍ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በእንጦጦ ፓርክ የላሊበላ ቨርቹዋል ሪያሊታ ዐውደ ርዕይ ተከፍቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጎብኝታቸውን አስታውሰው በላሊበላ ደግሞ ተመሳሳይ ዐውደ ርዕይ መከፈቱን ጠቅሰዋል።

በዩኔስኮ የተመዘገቡ የዓለም ቅርሶችን ማልማትና መጠበቅ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸው የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን የመጠበቅና የቱሪስት መዳረሻነቱን የማልማትና የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን መስህቦች የማልማት፣ የመጠበቅና የማስተዋወቅ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴታው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች፣ የጎንደርና የጅማ አባጅፋር አብያተ መንግሥታት ዕድሳትንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

በዘርፉ አቅም ለመገንባት የሰው ኃይል ስልጠና እና የቱሪስት የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የሆቴልና ቱሪዝም ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

በላሊበላ የተለመዱ የቱሪዝም ሀብቶችን ማሳየት ብቻ ሳይሆን የጎብኝዎችን ቆይታ የሚያራዘም የጉብኝት ፓኬጅ በመቅረፅና እሴት በመጨመር ተወዳዳሪ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ የሚያስችልና አካባቢያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ “የላሊበላ ዘላቂ ፕሮጀክት” እየተተገበረ መሆኑንም አንስተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የጊዜ ገደቡን ለመጠናቀቅ አንድ ዓመት ብቻ የቀረው የዘላቂ ልማት ፕሮጀክት ቀጣይ ምዕራፍ እንዲኖረውም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ሕይወት ኃይሉ፤ ቅርሶች ታሪክን ለመዘከር፣ ተፈጥሮና አካባቢን ለመረዳት ቅርስ የመረጃ ምንጭ በመሆንና የገቢ ምንጭነታቸው የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

ባለስልጣኑ ቅርሶች ለታሪክ ምስክርነት እንዲውሉ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ፣ ከጉዳት የመጠበቅ፣ የማጥናትና የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት ጥቅማቸውን የማሳደግና ተደራሽ የማድረግ ሥራዎችን ከባለድርሻ አካላት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በፈረንሳይ ልማት ኤጄንሲ ድጋፍ በ22 የትኩረት መስኮች ለይቶ የሚሰራው ‘የላሊበላ ዘላቂ ልማት’ ፕሮጀክት ትግበራም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል።

የላሊበላ ቋሚ ዐውደ ርዕይ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል የሚፈጥርና የጎብኚዎችን ቆይታ የሚያራዝም መሆኑን ገልፀው፣ በቀጣይም በሌሎች ቦታዎችም ይከፈታል ብለዋል።

ቅርስ መጠበቅና መንከባከብ የዜግነት ኃላፊነት ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሯ፣ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ዕድሳትና ጥገና እንዲሁም የቅርሶችን ጊዜያዊ መጠለያ የማንሳት ስራዎች በጥንቃቄ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አማራ ነን እንጅ አማራ እንሁን አላልንም” የዳንሻ ከተማ ነዋሪዎች
Next articleበሀገራዊ ምክክሩ ውስጥ የአማራ ሕዝብ በተገቢዉ መንገድ እንዲወከል መሥራት እንደሚያስፈልግ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን አስታወቀ።