“አማራ ነን እንጅ አማራ እንሁን አላልንም” የዳንሻ ከተማ ነዋሪዎች

137

ሁመራ: ግንቦት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ነዋሪዎች የማንነታቸው ጥያቄ በሕግ አግባብ እንዲጸድቅና ምላሽ እንዲሰጣቸው በሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እየጠየቁ ይገኛሉ።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ የዘር ማጽዳት፣ የማንነት ጭፍለቃ፣ የማሳደድና፣ የማፈናቀል ግፍና መከራ ሲደርስበት እንደቆየ ሰልፈኞቹ አንስተዋል።

ግፍና መከራው ያልበገረው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብም ስለማንነቱና ነፃነቱ ተዋድቋል፤ በርካቶች የሕይወት መስዋእትነትም ከፍለዋል።

መራራ ትግላችን ፍሬ አፍርቶ ነጻነታችን ከተጎናጸፍን ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ ኾኖናል ያሉት ነዋሪዎች የማንነት ጥያቄያቸው እውቅና እንዲሰጠው በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል።

በዳንሻ ከተማ አሥተዳደርም ሕዝባዊ ሰልፍ እየተካሄደ ሲሆን በሰልፉ ከተላለፉ መልእክቶች መካከል:

-አማራ ነን እንጅ አማራ እንሁን አላልንም!
-የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ የፍትሕ ወዳድ ኢትዮጵያዊያንም ጥያቄ ነው!
-የማይገባንን አልፈን አልጠየቅንም፤ የራሳችንንም አሳልፈን አንሰጥም!
-በማንነታችንና በርእስታችን አንደራደርም፣ የራሳችንንም አሳልፈን አንሰጥም!
-በወልቃይት ጠገዴ ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ፍትሕ እንፈልጋለን! የሚሉ መልእክቶች በሰላማዊ ሰልፉ ተስተጋብተዋል።

ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአርሶ አደሮች በሕገወጥ የግብርና ግብዓት አቅራቢዎች እንዳይታለሉ ግብርና ቢሮ አሳሰበ፡፡
Next articleየላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን የሚዘክር የአርኪኦሎጂና የቨርቹዋል ሪያሊቲ ቋሚ ዐውደ ርዕይ በላሊበላ ከተማ ተከፈተ።