የክረምት ፖለቲካ እና የዓባይ ውኃ ሰበብ!

117

ባሕር ዳር : ግንቦት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከተባረከው ማህጸኗ ለዘመናት ያለማቋረጥ ወጥቶ የፈሰሰው ውኃ ጸጋነቱ ለልጆቿ ሳይኾን ለጎረቤቶቿ ነበር፡፡ ዓባይን አልምቶ ለመጠቀም የነበረው ፍላጎት የመነጨው ቀደም ብሎ በነበሩ ነገሥታት ቢኾንም ምቹ ኹኔታ እና ብቁ አቅም ባለመኖሩ ፍላጎት እና እውነት ሳይገናኙ ዘመናት እንደጅረት ፈስሰዋል፡፡ ከዘመናት ብሶት እና እንጉርጉሮ በኋላ ዓባይ በማጀቱ ያድር ዘንድ እድል የሚሰጥ ክፍተት ተፈጠረ፡፡ የነገሥታቱ ፍላጎት እና የኢትዮጵያዊያን ቁጭት መጋቢት 24/2003 ዓ.ም ላይ ምላሽ አገኘ፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ለሕዝብ ይፋ ተደረገ፡፡

በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው እና ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያዊያን አንጡራ ሃብት የፈሰሰበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ምንም እንኳን በአምስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ቢባልም 10 ዓመታትን አስቆጥሮ እንኳን የግንባታው ሂደት ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም፡፡ ውጣ ውረድ እና ፈተና ርቋት የማታውቀው ኢትዮጵያ በፈተናዎች መካከል እያለፈች የምትገነባው ግድብ ዛሬ ላይ ቀድሞ የነበረውን የተሳሳተ እና መረን የለቀቀ የዓባይ ውኃ ባለቤትነት እሳቤ አቅጣጫ ቢያስቀይርም ጉዳዩ ሙሉ በሙሉ ተቋጭቷል የሚባል ግን አይደለም፡፡

የግንቦት ፖለቲካን ተገን ያደረጉ አንዳንድ የተፋሰሱ የታችናው ሀገራት እና ምዕራባዊያን ዞምቤዎቻቸው ክረምት በጠባ ደመና በዳመነ ቁጥር ኢትዮጵያ ላይ ያልተቋረጠ ጩኸት ማሰማታቸ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተዘወተረ የመጣ ነው የሚሉት የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካል-ኢኮኖሚ ተንታኝ ሎውረንስ ፍሪማን ናቸው፡፡ መርጦ ማልቀስን እንደ ፖለቲካ ስትራቴጂ የሚጠቀሙት አጋሮቻቸውም በግድቡ ላይ ደጋግመው የሰነዘሯቸው ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች ግድቡን ከግንባታ ባያስቆሙትም በብርቱው አልፈተኑትም ተብሎ ግን አይታሰብም ይላሉ ተንታኙ፡፡

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮች እና ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች እየተፈራረቁባት ከምጣኔ ሃብታዊ እስከ ዲፕሎማሲያዊ ፈተናዎችን አይታለች የሚሉት ሎውረንስ ፍሪማን በዚህ ሂደት ውስጥም ኾና ታላቅ ግድብ እና ታላቅ ታሪክ ሰርታለች ይላሉ፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በዓባይ ውኃ ላይ ከ5 ሚሊዮን ዓመታት በኋላ የታየ ታሪካዊ ክስተት ነውም ይላሉ፡፡ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ባለፈው ዓመት የመጎብኘት እድል እንደነበራቸው ያነሱት ሚስተር ፍሪማን “በአጽናፋዊ አድማስ ውስጥ የሰውን ልጅ ወሰን አልባ ተጽዕኖ በምናብ እንድመለከት አስገድዶኝ ነበር” ብለዋል፡፡

የግንቦት ፖለቲካ ሲረብሻት በኖረችው ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬም የዓባይ ውኃን ሰበብ አድርገው ችግር ለመፍጠር የሚጥሩ አልጠፉም የሚሉት የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኙ “በሚፈለገው ፍጥነት ልክ ባይኾንም እንኳን ግመሎቹ ከመጓዝ አልቆሙም” ይላሉ፡፡ ከሰሞኑ የአረብ ሊግን እንደ አዲስ የመጫዎቻ ካርድ የመዘዘችው ግብጽ አቅጣጫውን የቀየረ ተመሳሳይ ለቅሶ እና ጩኸት እንደኾነም ያነሳሉ፡፡ የምዕራቡ ዓለም ጣልቃ ገብነት በውስጥ ጉዳዮቻቸው ውጥረት ውስጥ መኾናቸውን ተከትሎ ተጸዕኖ መፍጠር አለመቻላቸው ፈርኦኖቹ የሴራ ፖለቲካ አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል ብለዋል፡፡

አቅጣጫውን ወደ አረብ ሊግ አባል ሀገራት ማዞሩ የሚሰማው ወቅታዊው የግብጽ አዲሱ የዓባይ ውኃ አስገዳጅ ውል ስምምነት የሚያመላክተው “የአፍሪካዊያንን ችግር በአፍሪካዊያን የመፍታት እሳቤን አሳንሶ ከማየት የመነጨ ነው” ያሉት ደግሞ የዓባይ ውኃ ጉዳይ ተመራማሪው ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ናቸው፡፡ በሀገራት መካከል ሥርዓት ያለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት የቆየ ነው የሚሉት ተመራማሪው ኢትዮጵያ ከበርካቶቹ የአረብ ሊግ ሀገራት ጋር በተናጠል መልካም የሚባል ግንኙነት እንዳላትም አንስተዋል፡፡ የአረብ ሊግ በተደጋጋሚ ያወጣውን ሚዛን የሳተ መግለጫ ኢትዮጵያ በዝምታ ያለፈችውም ይህንን የተናጠል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማክበር ነው ይላሉ፡፡

የዓባይ ተፋሰስ የታችኞቹ ሀገራት በተለይም ግብጽ እና ሱዳን ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የሚያሰሙት ድምጽ ወቅትን እና ኹኔታን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው የሚሉት የአፍሪካ ቀንድ ተንታኝ ሎውረንስ ፍሪማን ግብጽ የኢትዮጵያን ውስጣዊ ችግር እንደ መልካም እድል በመጠቀም ዲፕሎማሲያዊ ጫና ትፈጥራለች ብለዋል፡፡ እንደ ሎውረንስ ፍሪማን ገለጻ ሌላው የዓባይ ውኃን ሰበብ አድርጎ የሚሰማው የግብጻዊያን የክረምት ፖለቲካ መነሻው የግብጻዊያን የውስጥ ጫና እና ጥያቄ አቅጣጫ ለማስቀየሪያ ተደርጎም ይታሰባል ብለዋል፡፡

የኾነ ኾኖ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደቱን እያገባደደ ለተከታታይ ዓመታት ውኃ በመሙላት አሌክትሪክ ማመንጨት ጀምሯል፡፡ ግብጻዊያንም ይህንን ሃቅ ያውቁታል የሚሉት ሚስተር ፍሪማን ስጋታቸው እና ፍርሃታቸው ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት አልፋ ሌላ ፕሮጀክት ላለማምጣቷ እርግጠኛ አይደለንም ከሚል የነገ ስጋት የመነጨ ነው ይላሉ፡፡ ቱሪዝም፣ የዓሣ ልማት እና የኤሌክትርሪክ ኃይል ማመንጨት ከግድቡ የሚገኙ ጸጋዎች ሲኾኑ ለኢትዮጵያዊያን ነገም ሌላ ቀን ነው ይላሉ፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል ረቂቅ ዓዋጅ ተዘጋጀ።
Next articleበወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በማይካድራ እና በሁመራ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።