
ባሕር ዳር : ግንቦት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋ በሚከሰት መፈናቀል በዜጎች ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ጫና ለመቀነስ የሚያስችል የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ረቂቅ ዓዋጅ ተዘጋጀ።
በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ረቂቅ ዓዋጅ ዙሪያ ግብዓት ማሰባሰብ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ እናቶችና ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ዜጎች ተፈናቅለዋል።
ረቂቁ ዓዋጁ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በሚከሰት መፈናቀል ዜጎች የሚያስተናግዱትን ጫና ለመቀነስና ሕጋዊ በሆነ አግባብ ለመምራት ያስችላል ብለዋል።
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ምዝገባና ተያያዥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም እንዲሁ።
ረቂቁ ጸድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ለሀገር ውስጥ ለተፈናቃይ ዜጎች ተገቢው ሰብዓዊ የመብት ጥበቃና ሌሎች ድጋፎች እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል።
በፍትሕ ሚኒስቴር ዐቃቢ ሕግና የረቂቅ ዓዋጁ አርቃቂ ቡድን አባል ጠገነኝ ትርፌ ኢትዮጵያ የፈረመችው የአፍሪካ ኅብረት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ የካምፓላ ሥምምነት ለረቂቅ ዓዋጁ መነሻ መሆኑን ገልጸዋል።
መደረኩም ለረቂቁ ማጠናከሪያ ግብዓት ለማሰባሰብ እንደሚረዳ ጠቅሰው ዓዋጁ ሥራ ላይ ሲውል ተፈናቃይ ዜጎችን ችግር በማቃለል አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለዋል።
የምክክር መድረኩ ተሳታፊና የሕግ ባለሙያው ሰለሞን ወልደ-ገብርኤል፤ ለተፈናቃይ ዜጎች ጥበቃና ድጋፍ ለማድረግ ረቂቅ ዓዋጁ ተዘጋጅቶ ለአስተያየት መቅረቡ መልካም ጅምር መሆኑን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ሕግ መፈናቀልን መከላከል፣ ጥበቃ ማድረግ ወደ ቦታ መመለስን እንደሚደነግግ ጠቅሰው፤ ለተፈናቃይ ወገኖችም ተገቢ ክብር በመስጠት ዘላቂ መፍጥሄ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
የዋቻሞ የኒቨርሲቲ ፍልሰት ተመራማሪና ሌላኛው የምክክር መድረኩ ተሳታፊ ዶክተር ጸደቀ ላምቦሬ፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ የሕግ ድንጋጌ ባለመኖሩ ከቀያቸው ለሚፈናቀሉ ዜጎች ተገቢው ድጋፍና ጥበቃ ማድረግ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ረቂቅ ዓዋጅም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ በሚከሰት ፍልሰት የተፈናቀሉ ወገኖች በተቋማዊ አሰራር ለማገዝ ይረዳል ብለዋል።
በረቂቅ ዓዋጁ መሰረት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ብሔራዊ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ምክር ቤት እንደሚቋቋም ተጠቁሟል።
ምክር ቤቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሆኖ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትን፣ የኃይማኖት ተቋማትን፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችንና እንደአግባብነቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲካተቱ የሚደረጉ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ያቀፈ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
በመድረኩ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ተወካዮችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል። ዘገባው የኢዜአ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!