የብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ።

95

ባሕር ዳር : ግንቦት 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ማውሮ ቪዬራ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በነገው ዕለት አዲስ አበባ ይገባሉ።

በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ጃንዲር ፌሬራ ዶስ ሳንቶስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራ ልዑክ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በነገው ዕለት ኢትዮጵያ ይገባሉ።

ከቡድኑ ጋር የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ካርሎስ ዱዋርቴ አብረው ይመጣሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳፋኪ መሃመት ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪዬራ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋርም እንደሚወያዩ በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ጃንዲር ፌሬራ ዶስ ሳንቶስ አስታውቀዋል።

በጉብኝታቸው ብራዚል ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋሉ። በተለይ በግብርና፣ በጤና እና በማህበራዊ ፖሊሲዎች ላይ የሁለትዮሽ ትብብርን ለማስፋት ጉብኝታቸው ወሳኝ መሆኑንም አምባሳደር ጃንዲራ ገልጸዋል።

ብራዚል እና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚጋሯቸው ጉዳዮች አሉ። ኢትዮጵያ በድጋሚ በብራዚሊያ በዚህ ዓመት ኤምባሲዋን ከፍታለች።

እ.ኤ.አ.በ2022 በሁለቱ ሀገራት መካከል ከፍተኛ የሆነ የንግድ ልውውጥ ተደርጓል። ይህም ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። እ.ኤ.አ. በ2016 ፕሬዚዳንት ዲልማ ሩሴፍ የብራዚል ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ሚኒስትር ቪዬራ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሳይንስና ቴክኖሎጅ የፈጠራ ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጅ ኮሚሽን
Next articleለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል ረቂቅ ዓዋጅ ተዘጋጀ።