
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሳይንስና ቴክኖሎጅ የፈጠራ ሥራዎችን የሚያሳይ አውደ ርዕይ ተካሂዷል። በአውደ ርዕዩ 140 ተማሪዎችና መምሕራን በግብርና፣ በቴክኖሎጅ፣ በትራንስፖርትና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የሠሯቸውን የፈጠራ ሥራዎችን አቅርበዋል።
የፈጠራ ሥራቸውን ካሳዩት መካከል ከምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ በረንታ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪው ጌታቸው አባተ አንዱ ነው። ተማሪ ጌታቸው ባለሶስት እግር የፔዳል ባጃጅ ተሽከርካሪ ነው ለእይታ ያቀረበው። ወጣቱ እንዳለው የወዳደቁ ብረታብረቶችን በመሰብሰብ ነው በፔዳል የምትንቀሳቀስ ባለ ሦስት እግር ባጃጅ ሠርቶ ለእይታ ያቀረበው። ተሽከርካሪዋ ሁለት ሰዎችን የመጫን አቅም አላት። አሁን ላይ ለመጓጓዣነት ይጠቀምባታል።
በቀጣይም ከፔዳል የሶላር ኀይል ለመጠቀም እየሠራ መኾኑን ነግሮናል። ወጣቱ የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ባጃጅ ለእይታ ያቅርብ እንጅ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች ባለቤት መኾኑን ገልጿል።
የጀመረውን ፈጠራ በማሳደግ ወደ ትልቅ ድርጅት የመሸጋገር ሕልም እንዳለው ተናግሯል።
የአማራ ክልል ትምሕርት ቢሮ ኀላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ.ር) እንዳሉት የአሁኖቹ የፈጠራ ባለቤቶች በቀጣይ በዘርፉ ሀገሪቱን ካለችበት ችግር ለማውጣት መሠረቶች ናቸው። የፈጠራ ባለቤቶችን ለማበረታታት ትምሕርት ቢሮ የገንዘብና የሙያ ድጋፍ እያደረገ ይገኛልም ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲዎችና በባለሃብቶች እንዲደገፉ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። የተማሪዎችን ፈጠራ ለማጎልበት አዲሱ ሥርዓተ ትምሕርት በተግባር ተኮር እና በሀገር በቀል እውቀት ላይ እንዲያተኩር መደረጉንም አብራርተዋል። ለዚህ ደግሞ በትምሕርት ቤቶች ቤተ ሙከራዎችን እና የተሞክሮ ማዕከላት እንዲኖራቸው እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጅ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሌ አያሌው (ዶ.ር) የሳይንስና ቴክኖሎጅ የፈጠራ ሥራዎችን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የአዕምሯዊ ንብረትነት የሕግ ማዕቀፍም ወጥቷል፤ የፈጠራ ባለቤቶችን ለመደገፍ የሚያስችል የኢኖቬሽን ምክር ቤትም በፌደራል ደረጃ ተቋቁሟል ብለዋል።
በቀጣይ ባለሃብቶች ከፈጠራ ባለቤቶች ጋር እንዲሠሩ የሚደረግበት ሥርዓት እንደሚዘረጋ ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል። የተሻለ የፈጠራ ሥራ ላላቸው ደግሞ ሽልማትና ዕውቅና እንደሚሰጥ ገልጸዋል። የፈጠራ ባለሙያዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችላቸው ሥርዓት እንዲፈጠር እየተጠየቀ መኾኑንም አንስተዋል። የፈጠራ ባለቤቶችን አቅም ለማሳደግ መንግሥት ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ ባለሃብቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!