
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር የሚገኘው የሰሜን ምዕራብ እዝ መቀመጫ በሆነው መኮድ ካምፕ ውስጥ ሲከናወኑ የቆዩ የእድሳት ሥራዎች ዛሬ ተመርቀዋል። ከሥራዎቹ መካከል የሕንጻዎች እድሳት ይገኝበታል። 7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የግንብ አጥር ግንባታም ተጠናቅቋል።
በምርቃቱ ላይ የተለያዩ ጄነራል መኮንኖች ተገኝተዋል። የመከላከያ መሀንዲስ ዋና መምሪያ ኀላፊው ሌተናል ጄነራል ደስታ አብቼ፤ የመኮድ ካምፕ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አሉኝ ከሚላቸው ዋና ካምፖች ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል። በአያያዝ ችግር ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ካምፖች የመጠገን ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል። የመኮድ ካምፕም ሙሉ ጥገና እና አዳዲስ ሥራዎች ተሠርተውለት ለሠራዊቱ ምቹ እንዲኾን ተደርጓል ነው ያሉት።
ሌተናል ጄነራል ደስታ አብቼ “የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገርን ከመጠበቅ በተጨማሪ ትላልቅ ልማቶችን በመገንባትም እያገለገለ ይገኛል” ብለዋል። ለአብነትም ከግልገል በለስ እስከ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ድረስ የሚዘልቅ 220 ኪሎ ሜትር መንገድ ጠርጎ ማስረከቡን ገልጸዋል። አሁንም በዚያው አካባቢ የሚገኝ 110 ኪሎ ሜትር መንገድ ተረክቦ እየሠራ ሲኾን 40 ኪሎ ሜትሩ ተጠናቅቋል ነው ያሉት። በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ደግሞ ቀሪው እንደሚጠናቀቅ ተመላክቷል።
ሌላው በምርቃቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄነራል ብርሃኑ በቀለ፤ መከላከያ ሁልጊዜም የሚኖር ከሀገር ጋር ዘላቂ ተቋም ነው ብለዋል። ይህንን ተቋም እያጠናከሩ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚያስፈልግም መልዕክት አስተላልፈዋል።
መከላከያ በርካታ ተቋማት እንዳሉት የጠቀሱት አዛዡ፤ በየአካባቢው በርካታ የመምሪያ ካምፖች እንዳሉት ጠቅሰዋል። የእነዚህ ካምፖች ይዞታ በደንብ ተጠብቆ እና ባማረ መልኩ ተገንብቶ ለሠራዊቱ ምቹ እንዲሆን በሚደረገው እንቅስቃሴ የመኮድ ካምፕም ደረጃውን የጠበቀ እድሳት እንደተደረገለት አዛዡ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!