
ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ውኃ ሰማያዊዎቹ ከቀያይ ሰይጣኖቹ፤ የውድድር ዓመቱ የፕሪሜር ሊግ አሸናፊ ከካራባው ካፕ አሸናፊ ጋር ለሁለተኛ ዋንጫ ይገጥማሉ፡፡ ይህ ግጥሚያ በእግር ኳስ ቤተሰቡ ዘንድ እጅግ ተጠባቂ ነው፡፡ ግዙፉ የዌምብሌይ ስቴዲየም በ90 ሺህ ተመልካች ከአፍ እስከ ገደፉ ጢም ብሎ ተጠባቂውን የአንድ ከተማ ሁለት ክለቦች ታሪካዊ ፍልሚያ ያስተናግዳል፡፡
የ2023 የኤፍኤ ካፕ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ በማንቸስተር ሲቲ እና በማንቸስተር ዩናይትድ መካከል በኢትዮጵያዊያን ስዓት አቆጣጠር ዛሬ አመሻሽ 11 ስዓት ላይ ይጀመራል፡፡ የሁለቱ ክለቦች የምሽት ፍልሚያ ከአንድ ውድድር የዘለለ ብዙ ታሪካዊ መሠረቶች አሉት፡፡ በሀገሪቱ ርእሰ መዲና ሎንዶን የከተማው ግዙፉ ዌምብሌይ ስታዲየምም ይህንን ታሪካዊ ክስተት ያስተናግድ ዘንድ እድል አግኝቷል፡፡
የውኃ ሰማያዊዎቹ አለቃ ፔፕ ጋርዲዮላ የውድድር ዓመቱን በሦስት ዋንጫ ለማጠናቀቅ የሞት ሽረት ትግል ያደርጋሉ፡፡ በ2018/19 የውድድር ዓመት የፕሪሜር ሊጉን እና የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን ማሳካት የቻሉት አለቃ ጋርዲዮላ በ2022/23 የውድድር ዓመት ሦስት ዋንጫ በማንሳት የዩናይትዶችን ታሪክ መጋራት ይፈልጋሉ፡፡ ሰር አሌክሳንደር ቻፕማን ፈርጉሰን በ1998/99 የውድድር ዓመት የቻምፒዩንስ ሊግ፣ ፕሪሜር ሊግ እና ኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫዎችን በማንሳት በአንድ የውድድር ዓመት ሦስት ዋንጫ ክብረ ወሰን አላቸው፡፡
የቀያይ ሰይጣኖቹ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ የውድድር ዓመቱን በሁለት የሀገር ውስጥ ዋንጫ አጠናቀው የቀጣይ ዓመት ውድድር ቅድመ ዝግጅታቸውን ማሳመር ከመፈለጋቸው በላይ የክለባቸው የሦስት ዋንጫ ስኬት ክብረ ወሰን በምንጊዜም ተቀናቃኛቸው መጋራትን ፈጽሞ አይፈልጉም፡፡ ለዚህም ሲባል በአውሮፓ የቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሪያል ማድሪድን በማሸነፍ ለፍጻሜ የደረሠውን ማንቼስተር ሲቲ በማሸነፍ የሦስት ዋንጫ ሕልማቸውን ማምከን ይፈልጋሉ፡፡
ከነገረ ቀደም ከጨዋታ በፊት የቃላት ሽንቆጣ እና ጉሽሚያ የለመደው የእንግሊዝ እግር ኳስ ከወትሮው በተለየ መልኩ እጅግ መከባበር የበዛበት አስተያየት ከሁለቱ አሰልጣኞች ሲሰነዘር ተስተውሏል፡፡ “ሲቲ ጥሩ እየሠራ ይገኛል፤ አሁን የደረሱበት ደረጃም ይገባቸዋል” ያሉት የቀያይ ሰይጣኖቹ አሰልጣኝ ነገር ግን የእኛ ጥንካሬ ከተጋጣሚዎቻችን ድክመት እና ጥንካሬ የመነጨ አይደለም ብለዋል፡፡ በዛሬው ውድድር ብዙ ይጠበቅብናል ያሉት አሰልጣኙ ሲቲን ለማቆም ሳይኾን ለማሸነፍ እንደሚገቡም ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ ክለቦች የ15 ዓመታት የአሰልጣኝነት ዘመናቸው 11 ጊዜ የሊግ ዋንጫዎችን በማንሳት ተዓምራዊ ግስጋሴ እያደረጉ ያሉት አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላም የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ለሁለተኛ ጊዜ ከማንሳት የዘለለ ትርጉም ያለው ፍልሚያን ዛሬ ያደርጋሉ፡፡ “የዩናይትድ አሰልጣኝ የተለየ ነው፤ ዩናይትድም ከብዙ ዓመታት በኋላ ሙያችንን በተሻለ ደረጃ የሚያውቀውን አሰልጣኝ ያገኘ ይመስለኛል” ያሉት የውኃ ሰማያዊዎቹ አለቃ በዓለም ላይ እጅግ የተለየ የሆነውን የሀገር ውስጥ ዋንጫ በድጋሚ ለማንሳት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ሲቲ በአንድ የውድድር ዓመት ሦስት ዋንጫዎችን የማሳካት ህልሙን እውን አድርጎ የተቀናቃኙን ታሪክ ይጋራ ይኾን? ወይስ ቀያይ ሰይጣኖቹ የአይረሴውን አሰልጣኝ የሦስት ዋንጫ ታሪክ ያስጠብቃሉ? ዩናይትዶች የውድድር ዓመቱን በሁለት የሀገር ውስጥ ዋንጫ ይደመድማሉ? ወይስ ሲቲዎች የዛሬውን ውድድር አሸንፈው ለቻምፒዮንስ ሊግ ህልማቸው ይዘጋጃሉ፡፡ ሁሉም ዛሬ ምሽት በሎንዶን ምላሹን ያገኛል፡፡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለቱ የአንድ ከተማ ክለቦች በኤፍ ኤ ካፕ ፍጻሜ ፍልሚያ ዛሬ 11 ስዓት ላይ ይገናኛሉ፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!