በደብረ ታቦር ከተማ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ተመረቁ።

49

ደብረ ታቦር፡ ግንቦት 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከዓለም ባንክ በተገኘ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ ኾነዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች በገንዘብና በጉልበት ድጋፍ በማድረግ በአጭር ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ አሥተዋጽኦ ማድረጋቸው በምርቃ ሥነሥርዓቱ ተገልጿል።

ከተመረቁ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ 4 ነጥብ 5 ኪ/ሜ ጌጠኛ ድንጋይ መንገድ፣ ተፋሰሶች ጥገና እና በአዲሥ የተሠራ 10 ነጥብ 8 ኪ/ሜ ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራውን የሚያቀላጥፉ ከ 6 በላይ ሸዶች፣ የጥርጊያ መንገድ እና 11 ነጥብ 5 ኪ/ሜ በላይ ርዝመትና 10 ሜትር ሥፋት ያለው የጠጠር መንገድ፣ 10 ክፍል ያለው የቀበሌ ቤት እና 5 ነጥብ 4 ኪ/ሜ የውኃ መሥመር ኪ/ሜ የሚጠቀሱ ናቸው።

የከተማዋ ነዋሪዎች መሠረተ ልማቶቹ ከዚህ በፊት በከተማዋ ከመሠረተ ልማት ተደራሽነት ጋር ያነሷቸው የነበሩ ችግሮች መሆናቸውን ገልጸው በተለይ የክረምት ወቅት መግቢያ ላይ ተጠናቀው ለአገልግሎት መድረሳቸው ችግሮቻቸውን እንደሚያቀልላቸው ተናግረዋል። ከዚህ በፊት ተጀምረው የማይጠናቀቁ መሠረተ ልማቶች የሕዝብን ሥሜት የሚጎዱ ነበሩ ያሉት ነዋሪዎቹ በአጭር ጊዜ በጥራት ተሠርተው መድረሳቸው በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎች የሚጠይቋቸው መሠረተ ልማቶች ላይ ተሥፋ እንዲያደርጉና ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያሥችሉ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

በምረቃ ሥነሥርዓቱ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤን ጨምሮ የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ እንዲሁም የዞን የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ጻድቁ አላምረው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል ወረዳዎች መጋዝን ውስጥ የተቀመጠ የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነት ለአርሶ አደሩ በፍትሀዊነት እንዲሠራጭ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
Next articleበመካነ ሰላም ከተማ የተከሰተ ድንገተኛ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን የከተማዋ ፖሊስ ገለጸ።